የሕክምና አገልግሎት ጥራትን በማሳደግ አምራች ዜጋ የማፍራት ተግባራት ይጠናከራል – እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የሕክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት በማሳደግ ጤናማና አምራች ዜጋ የማፍራት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ።
‘በባለቤትነት ላይ የተመሰረተ ዕውቅናና ተጠያቂነት ለጠንካራ ጤና ስርዓት ግንባታ’ በሚል መሪ ሀሳብ በቡታጅራ ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የክልሉ የ2017 ዓመታዊ የጤና ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል፡፡
እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በጉባኤው ማጠቃለያ መድረክ ላይ እንዳሉት፤ ጠንካራ የጤና ስርዓትን ለመገንባት ፖሊሲና ፕሮግራሞችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል፡፡
ለዚህም የጤና ባለሙያውን ለማብቃት፣ የተቋማትን ዲጂታል አሰራር ለማሳደግ እና በጤና ተቋማት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ይሰራል ብለዋል።
የዘርፉን አገልግሎት ማዘመን የማህበረሰቡን እርካታ ስለሚያሳድግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ገልጸው፤ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን በማሳደግ ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራት የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ አረጋግጠዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሰሃርላ አብዱላሂ በበኩላቸው፤ የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ የጤና አገልግሎቱን ለማስፋትና ዲጂታላይዝ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
የጤና ተቋማትን የሪፎርም ሥራ ተግባራዊ ከማድረግ ባለፈ ባለሙያውን የማብቃት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በ2017 በጀት ዓመት የጤና ተቋማትን የወሊድ አገልግሎት ማሻሻልን ጨምሮ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ናቸው።
የሕክምና አገልግሎትን ለማሻሻል በተሰራው ሥራ 33 የአልትራሳውንድ ሕክምና መስጫ መሳሪያዎች መገዛታቸውን ጠቅሰዋል።
የመድሃኒት አቅርቦት ውስንነቶችን ለመፍታት ከ550 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመድሃኒት ግዥ መፈጸሙን ገልጸው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ማህበረሰቡን በማሳተፍ የተሟላ የህክምና አገልግሎትን ለመስጠት እንደሚሰራ ተናግረዋል።