በዲዮጎ ጆታ ስም ለማህበረሰብ ተኮር ተግባራት ከ225 ሺህ ፓውንድ በላይ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሊቨርፑል በዲያጎ ጆታ እና በወንድሙ አንድሬ ጆታ ስም ለሚከናወኑ ማህበረሰብ ተኮር ተግባራት የሚውል ከ225 ሺህ ፓውንድ በላይ ገቢ መሰብሰቡን ይፋ አድርጓል፡፡
ሊቨርፑል ገቢውን የሰበሰበው ለዲያጎ ጆታ መታሰቢያ ከተዘጋጁ ህትመቶችና ቲሸርቶች ሽያጭ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ገንዘቡ በሊቨርፑል ፋውንዴሽን በኩል ለዲያጎ ጆታ መታሰቢያ ለሚደረጉ የማህበረሰብ ተኮር የእግር ኳስ ፕሮግራሞች ድጋፍ እንደሚውል ተመላክቷል፡፡
በዚህም በዲያጎ ጆታ ስም የሚሰየሙ የእግር ኳስ ሜዳዎች እንደሚገነቡ የተገለጸ ሲሆን፥ እስካሁን ድረስ በድምሩ 226 ሺህ 995 ፓውንድ መሰብሰብ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡
የቀድሞ የሊቨርፑል ተጫዋች ዲያጎ ጆታ እና ወንድሙ አንድሬ ጆታ በመኪና አደጋ ሕይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ሲሆን፥ ሊቨርፑልም የጆታን ቀሪ ደመወዝ ለቤተሰቡ እንደሚሰጥ መግለጹ አይዘነጋም፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ