በኦሮሚያ ክልል ህዝብና መንግስት በሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ተናብቦ የመሥራት ዝንባሌ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ መንግስት ገለፀ
አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልሉ ህዝብና መንግስት በሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ተናብቦና ተመካክሮ የመሥራት ዝንባሌ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል፡፡
ለሀገሪቷ ህዝቦች የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀውና ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ የጀመረው ሁለንተናዊና ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለአንድም ሰከንድ እንዳይጨናገፍ ዘብ የመቆምና የማከናወኑ ሂደት ልዩ ትኩረት አግኝቷልም ነው ያለው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከቀበሌ እስከ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ያሉ መዋቅሮችና መላ ህዝቡ በዚህ ወር ሲያካሂዱ በነበረው የሠላም ኮንፈረንስ አንድ ፅኑ አቋም ላይ ደርሰዋል ያለው መግለጫው የሠላም፣ የዴሞክራሲ፣ የልማትና የአብሮነት እሴቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና በፅኑ መሠረት ላይ እንዲቆሙ ሁሉም የድርሻውን ለመወጣት መወሰኑንም ነው ያስታወቀው፡፡
ከዚህ በተቃራኒ የህዝቡን ሠላም ለማወክና የለውጥ ግስጋሴውን ጠልፎ ለመጣል የሚታትሩ ኃይሎች ከቻሉ ለአፋቸው ልጓም ለድርጊታቸው ገደብ እንዲያበጁ ሀገራዊ ጥሪ ማስተላለፋቸውንም አውስቷል፡፡ ይህ ካልሆነ መንግሥት ህገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱንና ግዴታው የሆነውን የህግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ እንዲተገብር በሙሉ አቅማቸው ከጎኑ ለመሰለፍ ቃላቸውን አድሰዋልም ብሏል፡፡ በየደረጃው ያለው መዋቅርም ጥሪያቸውን ተቀብሎ በተደራጀ መልኩ እንዲያሰልፋቸው መላ ህዝቡ በአጽንኦት ማሳሰቡንም አንስቷል፡፡
ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት መሰል ጥሪዎች ተላልፈው እንደከሸፉ ሁሉ ሰሞኑን በስመ ቄሮ የሚነዛው የሁከትና ብጥብጥ ጥሪ ይህን የህብረተሰብ ክፍል የማይወክል መሆኑን ለማስታወስ እንሻለንም ነው ያለው፡፡ በዚህ አጋጣሚ መንግስት የፀረ ሠላምና ለውጥ አደናቃፊ ኃይሎችን ጥሪ በማክሸፍ ሂደት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ለነበራቸው መላ ህዝቡና የፀጥታ ኃይሉ ምስጋናውን እንደሚያቀብም ገልጿል፡፡
በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኘው ወጣትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በዚህ ወቅት የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና የዕለት ተዕለት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ተግባራቸውን በማከናወን ላይ መሆናቸውንም አትቷል፡፡ ስለሆነም ለፀረ ሠላምና ልማት ጥሪ የሚሰጡት ጆሮና ደቂቃ እንደማይኖራቸውም ነው የገለጸው፡፡
ይህ ወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታ የማይገደውና የተደላደለ ኑሮ እየኖረ ያለው ጥቂት ኃይል ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በሚዲያ ላይ በሬ ወለደ አሉባልታና የግጭት ነጋሪት በመጎሰም ላይ ይገኛል ያለው መግለጫው ከዚህ ጋር ተያይዞ ህዝቡ በልማት ላይ ተጠምዶ በሚገኝበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የፀጥታ አስከባሪ ኃይል የህብረተሰቡን ሠላም ለመጠበቅና ሁለንተናዊ ፀጥታ ለማረጋገጥ በሙሉ ዝግጅትና ቁመና ላይ እንደሚገኙም ጠቅሷል፡፡
ስለዚህ መላ ህዝቡ መደበኛ የልማት ሥራውን ከማከናወን ጎን ለጎን በአካባቢው የሚታዩ ለሠላምና ሠላማዊ እንቅስቃሴ ሥጋት የሆኑ ማናቸውንም ምልክቶች ለሠላም ኃይሉ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበርም ጥሪውን አቅርቧል፡፡