ከእንጦጦ ፓርክ የመብራት ገመዶችን የሰረቁ እስከ 23 ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ የወንጀል ጉዳዮች ችሎት ከእንጦጦ ፓርክ የመብራት ገመዶችን በመቁረጥ የስርቆት ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች እስከ 23 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወሰነ።
ችሎቱ የግራ ቀኝ ማስረጃ መርምሮ ተከሳሾቹን በተደራራቢ ክሶች ጥፋተኛ በማለት በየመዝገብ ደረጃቸው በጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።
ተከሳሾቹ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተማዎች ነዋሪ የሆኑት መልካሙ ማቲዎስ፣ ቢኒያም ካሳሁን፣ ደረጄ ተሰማ፣ ቶፊቅ ዓለሙ፣ አማኑኤል አቡ፣ አስመላሽ ትግስቱ እና በሌለበት ጉዳዩ የታየው ዓለሙ ተመስገን ናቸው።
የፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የጉለሌ ቅርጫፍ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር (1) ሀ እና የቴሌ ኮሙኒኬሽን እና የኤሌክትሪክ ሀይል አውታሮችን ለመጠበቅ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 464/97 አንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፋቸውን ጠቅሶ ተደራራቢ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸዋል።
በዚህም ተከሳሾቹ በየደረጃው በተለያዩ ጊዜ በሌሊት እንጦጦ ፓርክ ግቢ ውስጥ ንብረትነቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የሆነ ለመብራት አገልግሎት እንዲውሉ የተዘረጉ የኤሌክትሪክ ገመዶችን በተለያዩ ቀናት እየቆረጡ በተሽከርካሪ በመጫን ሰርቀው በመውሰድ ሸጠው በመከፋፈል ተግባር ተሰማርተው እንደነበር በክሱ ተመላክቷል።
በጥቅምት 4 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው እንጦጦ ሲኒማ ላይ በ4ኛ ተከሳሽ መሪነት 5ኛ ተከሳሽ ደግሞ የኤሌክትሪክ ገመድ መቁረጫ የብረት መጋዝ በመያዝ 3ኛ ተከሳሽ በሚያሽከረክረው ኮድ1 ላዳ ተሽከርካሪ ለእንጦጦ ፓርክ አገልግሎት እንዲውል የተዘረጋ የኤሌክትሪክ ገመድ ቆርጠው ሊወስዱ ሲሉ በፀጥታ አካላት የተያዙ በመሆኑ በፈጸሙት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የኤሌክተሪክ አውታር ስርቆት ሙከራ ወንጀል ተከሰዋል።
ከተከሳሾቹ መካከል መልካሙ ማቲዎስ የተባለው ተከሳሽ 7 ተደራራቢ ክስ የቀረበበት ሲሆን÷ ቀሪዎቹ ደግሞ ከ2 እስከ 3 ተደራራቢ የክሶች ቀርቦባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ መርምሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ሲሆን፤ ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮና ይዞ ወንጀሉ የተፈጸመው የሀገር ኃብት በሆነ መሰረተ ልማት ላይ በቡድንና በስምምነት፣ በሌሊት መሆኑን ማክበጃ በመያዝ 1ኛ ተከሳሽ መልካሙ ማቲዎስን ጥፋተኛ በተባለባቸው በ7 ክሶች ማለትም በእያንዳንዱ መዝገብ 3 እና 5 ዓመት ቅጣት በአጠቃላይ በድምሩ 23 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።
ቀሪ ተከሳሾች ደግሞ በየደረጃው ጥፋተኛ በተባሉባቸው ተደራራቢ መዝገቦች በያንዳንዱ መዝገብ ሲደመር ከ9 እስከ 6 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።
በታሪክ አዱኛ