Fana: At a Speed of Life!

የተቋማትን አቅም በማሳደግ ተወዳዳሪ የሳይበር ምህዳር መገንባት ያስፈልጋል – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማኅበረሰቡን ንቃተ ህሊና እና የተቋማትን አቅም በማሳደግ ተወዳዳሪ የሳይበር ምህዳር መገንባት ያስፈልጋል አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።
በክልሉ 6ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ‘የሳይበር ደህንነት – የዲጂታል ኢትዮጵያ መሰረት’ በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ የንቅናቄ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ነው።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ጥቅምት ወርን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ማጎልበቻ ወር በማድረግ ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ እያከበረ ይገኛል።
በዚህም ከአማራ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመተባበር የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የንቅናቄ መርሐ ግብሩ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
አቶ አረጋ ከበደ በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የቴክኖሎጂ ልማት ሀገራችን ልዩ ትኩረት የሰጠችው ዘርፍ ነው።
በመሆኑም የማኅበረሰቡን ንቃተ ህሊና እና የተቋማትን አቅም በማሳደግ ተስተካካይነትና ተወዳዳሪነት ያለው የሳይበር ምህዳር መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
የክልሉ መንግሥትም ተቋማትን የማደራጀት፣ የህግ ማዕቀፎችን የማዘጋጀትና የቴክኖሎጂ ልማት ስትራቴጂዎችን ማጽደቅ እንዲሁም ተቋማት አሠራራቸውን እንዲያዘምኑ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚዲ በበኩላቸው፤ የሳይበር ምህዳር ደህንነትን በማረጋገጥና የመከላከልና የማጥቃት አቅምን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የቴክኖሎጂ ምርቶችና መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
ተቋሙ የስማርት ከተማ ፕሮጀክቶችን ውጤታማ ለማድረግ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ሳይበርና ቴክኖሎጂ መር የሆነ ፈጣንና ውጤታማ የተቋማት አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂን በውጤታማነት ለመፈጸም በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በደሳለኝ ቢራራ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.