የአመቱ ምርጥ ፈራሚ እየተባለ የሚገኘው ግራኒት ዣካ…
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአንድ ወቅት በነውጠኝነቱ የሚታወቀውና በአሁን ሰዓት የሰንደርላንድ ስኬት መሪ ተዋናይ የሆነው ስዊዘርላንዳዊው ግራኒት ዣካ፡፡
በፈረንጆቹ 1992 በባዜል ስዊዝርላንድ የተወለደው ግራኒት ዣካ የእግር ኳስ ህይወቱ ጅማሮውን በዛው በትውልድ ከተማው ክለብ ባዜል አደርጓል፡፡
በባዜል ቆይታው ሁለት ጊዜ የስዊዝ ሻምፒዮን መሆን የቻለው ዣካ በ2012 ወደ ጀርመኑ ቦሩሺያ ሞንቼንግላድበህ አምርቷል፡፡
በግላድባህ ቆይታው በቴክኒካዊ ክህሎቱና የአመራር ሰጪነት ብቃቱ የተወደሰው ዣካ ቡድኑን በአምበልነት በመምራት ሁለት ጊዜ የሻምፒየንስ ሊግ ቦታን አንዲያገኝ አስችሏል፡፡
በ2016 በ30 ሚሊየን ፓውንድ የሰሜን ለንደኑን ክለብ አርሰናል የተቀላቀለው ዣካ በመድፈኞቹ ቤት ለሰባት አመታት ያህል ቆይታ አድርጓል፡፡
በመድፈኞቹ ቤት ቆይታው 300 ጨዋታዎችን በማድረግ ሁለት ጊዜ የኤፍኤ ዋንጫን ሲያሸንፍ ቡድኑንም በአምበልነት መምራት ችሏል፡፡
በአርሰናል ቆይታው አምስት ጊዜ የቀጥተኛ ቀይ ካርድ ሰለባ የሆነው ዣካ በአመራር ብቃቱና ቴክኒካዊ ችሎታው ቢደነቅም በብስጩ ባህሪው ከፍተኛ ትችት አስተናግዷል፡፡
ለአብነትም በ2019 ከቡድኑ ደጋፊዎች ጋር በግልጽ ግጭት ውስጥ በመግባት አርሰናልን ለመልቀቅ ወስኖ የወቅቱ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ አግባብተው ሀሳቡን እንዳስቀየሩት ዣካ ይናገራል፡፡
ከዛ ወዲህ ክለቡን እስከለቀቀበት ጊዜ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች በመሆን ከደጋፊዎች ዳግም ፍቅርንና ክብርን ማግኘቱ ይታወሳል፡፡
በ2023 ዳግም ወደ ጀርመን በመመለስ ለባየር ሊቨርኩሰን ፊርማውን ያኖረው ግራኒት ዣካ፥በመጀመሪያው አመት ሊቨርኩሰን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የቡንደስሊጋውን ዋንጫ እንዲያሸንፍ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡
ባለፈው ክረምት በ13 ሚሊዮን ፓውንድ ከጀርመኑ ክለብ ሊቨርኩሰን ሰንደርላንድን የተቀላቀለው ግራኒት ዣካ በአሁን ሰዓት የጥቋቁር ድመቶቹ ወሳኝ ተጫዋች ነው፡፡
ከስምንት አመታት ቆይታ በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው የኒውካስል ከተማው ክለብ የሊጉ ክስተት በመሆን አስደናቂ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል፡፡
ቡድኑ እጅግ የተደራጀ፣ ግቦች በቀላሉ የማይቆጠሩበትና ግቦችን የሚያስቆጥር በመሆን በ10 የሊጉ ጨዋታዎች 18 ነጥብ በመሰብሰብ የከተማ ተቀናቃኙ ኒውካስል ዩናይትድን ጨምሮ ቼልሲ፣ ማንቼስተር ዩናይትድና ቶትንሃም ሆትስፐር የመሳሰሉ ክለቦችን በመብለጥ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በዚህ የሰንደርላንድ የስኬት ጉዞ ውስጥ የዣካ ሚና ከፍተኛ ሲሆን፥ ሶስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ሲያቀብል አንድ ግብ አስቆጥሯል፡፡
ከዚህም በላይ ለቡድኑ ወጣት ተጫዋቾች ልምዱን በማካፈልና አመራር በመስጠት እየሰራ ያለው ስራ ከበርካቶች ሙገሳን አጎናጽፎታል፡፡
የሊቨርፑል የቀድሞ ተከላካይ ጄሚ ካራገር የዣካን ያህል ባለበት ክለብ ተጽዕኖ ያሳረፈ አዲስ ፈራሚ እንደሌለ በመግለጽ፥ ያለምንም ጥርጥር ለእኔ የአመቱ ምርጥ ፈራሚ ነው ብሏል፡፡
የሰንደርላንድ ቀንደኛ ደጋፊዎች በዘመናቸው እንደ ግራኒት ዣካ አይነት ድንቅ ተጫዋች በክለባቸው ሲጫወት አይተው እንደማያውቁ በመግለጽ እድለኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የ33 አመቱ የስዊዝርላንድ ብሄራዊ ቡድንና የሰንደርላንድ አምበል ዣካ ጥቋቁር ድመቶቹ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን እንዲያልሙ ያስቻለ ተጫዋች ሆኗል፡፡
በአቤል ነዋይ