Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን ድንቅ ባሕላዊ እሴቶችና ትውፊቶችን ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጠቀም ይገባል – ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ድንቅ ባሕላዊ እሴቶችና ትውፊቶችን ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጠቀም ይገባል አሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፡፡

ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ በርካታ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ኪነ ጥበባዊ ጸጋዎች እንዳሏት ገልጸው÷ እነዚህም የማንነታችን መገለጫ፣ የአንድነት ማሳያና የሕብረታችን ምልክት ናቸው ብለዋል፡፡

ብዝሃ ብሄር፣ ባህልና ቋንቋ የኢትዮጵያ መገለጫ ነው ያሉት ወ/ሮ ሸዊት÷ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ሁለንተናዊ አብሮነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ የሀገራችንን አንድነትና እና ሉዓላዊነት የሚፈታተኑ ችግሮች ሲመጡ በሕብረት የምንመክት ኩሩ ሕዝቦች ነን ሲሉም አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ድንቅ ባህላዊ እሴቶችና ትውፊቶች ያሏት ሀገር መሆኗን ገልጸው÷ ለአብነትም የተጣሉ የሚታረቁበት ሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓት እንዲሁም ወዳጅ ዘመድ የሚጠያየቅባቸው ክዋኔዎችን ጠቅሰዋል፡፡

ጥበባትና ባሕል የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማጠናከር እንዲሁም አብሮነትና አንድነትን ይበልጥ ለማሳደግ ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው አስገንዝበዋል፡፡

ስለሆነም ያሉንን ድንቅ ባሕላዊ እሴቶች በኪነ ጥበብ አዋዝቶ በማቅረብ የምንፈልጋትን ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ለመገንባት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ለዚህም ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የሕዝቦችን አብሮነትና ትስስር የሚያጎለብቱ ሥራዎችን በመከወን የበኩሉን ሚና መወጣት ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡

አሁን ላይ ኪነ ጥበብን በመጠቀም ገዢ ትርክትን ለማስረጽና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የተጀመሩ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል፡፡

በዚህ ረገድ የኪን ኢትዮጵያ እና የሃገር ሽማግሌዎች ልዑክ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው÷ በቀጣይ የኪን ኢትዮጵያ አባላት በሀገሪቱ ትላልቅ ከተሞች ትስስርን የሚያጠናከሩ ሥራዎችን እንደሚያከናወኑ አብራርተዋል፡፡

ታላቅና ገናና የሆነች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሻገር ባህላዊ እሴቶችና ትውፊቶችን ማልማት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ባህል በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት ውስጥ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው÷ ብዝሃ ባህል ሃብቶችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.