የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማትን ለማጠናከር ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማትን በማጠናከር ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው አለ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን፡፡
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ነው፡፡
በመርሐ ግብሩ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ እና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ በዚህ ወቅት ÷ ተፈጥሮ ለኛ ከተሰጠ ሀብትነት ባሻገር ለመጪው ትውልድ የምናስተላልፈው አደራ ጭምር ነው ብለዋል፡፡
የተፈጥሮ ሃብትን መጠበቅ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን ገልጸው ÷ ተራሮች፣ ሰፋፊ ወንዞች፣ ረግረጋማ ቦታዎች፣ ጥልቅ ሸለቆዎች እና ሐይቆች የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ሃብት መለያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ዋልያ አይቤክስ፣ ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ እንዲሁም በርካታ አዕዋፋትና አበቦች በተፈጥሮ ሃብታችን የታደልናቸው የሀገራችን ማንነት እና የኢኮኖሚያችን አቅም ናቸው ሲሉም አውስተዋል፡፡
የዱር ሕይወት ጥበቃ በኢትዮጵያ ከዘመናዊ ተቋማዊ አደረጃጀት በፊት በባሕላዊና ማህበራዊ እሴቶቻችን ውስጥ ዘመን የተሻገረ፣ ስር የሰደደና የማሕበረሰብ ጥበቃ ተሞክሮዎች ለዛሬው ጥበቃ መሰረቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
ከ60 ዓመታት በፊት በሁለት ብሔራዊ ፓርኮች የተጀመረው ዘመናዊ የጥበቃ ጉዞ ዛሬ ላይ እንደ ሀገር ከ30 በላይ መድረሱን እንዲሁም በርካታ የዱር እንስሳት መጠለያዎች ከ106 በላይ ልዩ ልዩ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች መፈጠራቸውን ተናግረዋል፡፡
ዛሬ እንደ ሰፊ የጥበቃ ቦታዎች አስተዳደር፣ የብሔራዊ ፓርኮች ልማት፣ የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ፣ ዘላቂ ቱሪዝም እና የማሕበረሰብ ተሳታፊነት የተመሰረተበትን ልማት ማረጋገጥ እንደተቻለ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡