ለምርጫው ስኬታማነት ሴቶች በግንባር ቀደምነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን ሴቶች በግንባር ቀደምነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል አሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ።
የሰላም ሚኒስቴር ከሴቶች አደረጃጀት ጋር በመተባበር ‘ለሰላማዊ ምርጫ የሴቶች ሚና’ በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የማጠቃለያ መድረክ አካሂዷል።
አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ እንዳሉት፤ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን እና ዴሞክራሲ እንዲያብብ ሴቶች በመራጭነት፣ በተወዳዳሪነት እና የሰላም ዘብ በመሆን አሻራቸውን በግንባር ቀደምነት ሊያኖሩ ይገባል።
በለውጥ ማግስት ሴቶች በመንግሥት ስልጣን ከ50 በመቶ በላይ ድርሻ እንዲኖቸው በማድረግ ዓለም አቀፍነት ያለው ተምሳሌትነት ተመዝግቧል ብለዋል።
በኮሪደር ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት እና በመሳሰሉት ሴቶች የመንግሥት ኢኒሼቲቮች ግንባር ቀደም ተጠቃሚና ተሳታፊ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
ቁልፍ የውሳኔ ሰጪ ተቋማት በሴት አመራሮች እንዲመሩ መደረጋቸው የለውጡን ፍሬያማነት ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የመምረጥና የመመረጥ መብትን በመጠቀም ሴቶች የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የምርጫውን ሰላማዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ከማስቻል አንጻር ሴቶች የጎላ ሚና እንዳላቸውም አመልክተዋል።
ወጣቱ በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ የማስተማር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።