በረመዳን ወቅት የታየው የመረዳዳትና መተሳሰብ እሴት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል – ሼህ አብዱልከሪም ሼህ በድሪን
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በረመዳን ጾም ወቅት የነበረው የመረዳዳትና መተሳሰብ እሴት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል አሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱልከሪም ሼህ በድሪን።
ሼህ አብዱልከሪም ሼህ በድሪን 1ሺህ 447ኛውን የዒድ አልፈጥር በዓል አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመጠየቅ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በረመዳን የጾም ወቅት የነበሩት እርስ በርስ የመደጋገፍ፣ መረዳዳትና መተሳሰብ እሴቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በተለይም በዓሉን በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ በማድረግና አብሮነትን በማሳየት ማሳለፍ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የዒድ አልፈጥር በዓልን ሕዝበ ሙስሊሙ ሐይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የዘንድሮው የዒድ አል ፈጥር በዓል ጨረቃ ዛሬ ማታ መጋቢት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ከታየች ሐሙስ መጋቢት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ይከበራል፡፡
ጨረቃ ዛሬ ማታ ካልታየች ደግሞ በዓሉ መጋቢት 11 ቀን 2018 ዓ.ም የሚከበር መሆኑን ሼህ አብዱልከሪም ሼህ በድሪን በሰጡት በመግለጫ አመልክተዋል፡፡
በጌታሰው የሽዋስ