በክልሉ የትንሳዔ በዓል የፍጆታ ምርቶች እጥረት እንዳይከሰት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መጪውን የትንሳኤ በዓል ተከትሎ የፍጆታ ምርቶች ላይ እጥረት እንዳይከሰት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል አለ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ።
የቢሮ ኃላፊ አቶ ታሪኩ አካሉ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በፍጆታ እቃዎች ላይ ሰው ሰራሽ የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠርና የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር በክልሉ በሚገኙ ሁሉም መዋቅሮች ዝግጅት ተደርጓል።
በዚህም ለበዓል አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች በብዛት ወደ ገበያዎች እንዲቀርቡ ከአምራቾችና አቅራቢዎች ጋር የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
በየደረጃው ያሉ የሕብረት ሥራ ዩኒየኖችና መሰረታዊ ማሕበራት ለበዓል ገበያ ተፈላጊ ምርቶችን በተለይም ጤፍ፣ ሽንኩርት፣ እንቁላል፣ ዶሮ፣ ቅቤ፣ ቲማቲም፣ የእርድ እንስሳት እና ፍራፍሬ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲያደርጉ መሰራቱን ጠቁመዋል።
ሸማቹ ማሕበረሰብ ከአምራቾችና ከጅምላ አቅራቢ ነጋዴዎች ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገዙ የቅዳሜና እሑድ እንዲሁም ሌሎች ተደራሽ ገበያዎችን የማመቻቸት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ በሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ለመከታተልና ርምጃ ለመውሰድ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በየደረጃው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ሕብረተሰቡ በበዓል ወቅት ያለውን ፍላጎት ምክንያት በማድረግ የሸቀጦችን ዋጋ የሚያንሩ ስግብግብ ነጋዴዎችን በየአቅራቢያቸው ለተሰማሩ ተቆጣጣሪ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።
በአድማሱ አራጋው