ሕብረተሰቡ በእርድ ወቅት የቆዳና ሌጦ ምርቶች እንዳይበላሹ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብርና ሚኒስቴር ሕብረተሰቡ በእርድ ወቅት የቆዳና ሌጦ ምርቶች እንዳይበላሹ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠየቀ።
በሚኒስቴሩ የስጋና ቆዳ ሀብት ልማት ዴስክ ኃላፊ አቶ አስመላሽ በርሄ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ እንደሀገር በየዓመቱ በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር የቀንድ ከብት ቆዳ፣ የበግ እና የፍየል ሌጦ ይመረታል።
ይሁን እንጂ በጥራትና በብዛት ተሰብስቦ ለገበያ የሚደርሰው ቁጥር ከሚመረተው አንጻር ሲታይ አነስተኛ መሆኑን ገልጸው÷ ለዚህም የሽያጭ ዋጋ መቀነስና ግንዛቤ ክፍተት መኖሩን እንደምክንያት አንስተዋል።
ቆዳና ሌጦ ለኢኮኖሚ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለተለያዩ ባህላዊ አገልግሎቶችና ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ አቅም እንዳለውና ይህንንም በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመጪው የትንሣኤ በዓል በርካታ የእንስሳት እርድ የሚከናወን በመሆኑ በቅድመ እርድ፣ እርድና ድህረ እርድ ወቅቶች የሚፈጠሩ የቆዳና ሌጦ የጥራት ጉድለቶች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በዚህም መሰረት ለዕርድ የሚቀርቡትን እንስሳት በዱላ አለመምታት፣ የሚታረዱበትን ቦታ ንፁህ ማድረግ እና ለእርድ ሲጣሉ ከመሬት ጋር አለማጋጨት፣ ሲታረዱ ደማቸው ተሟጦ እንዲወጣ ማድረግ፣ ቆዳው ሲገፈፍ ቅርፅን መጠበቅና በአሰነዛዘር ወቅት የተፈጥሮ መስመርን ተከትሎ መሰንዘር እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
እንዲሁም ቆዳው ሲገፈፍ እንዳይቀደድና እንዳይበሳ ጥንቃቄ ማድረግ፣ ቆዳ ሲሰበሰብ መሬት ላይ አለመጎተት፣ አለማቆሸሽ እና በርጥበት እንዳይበሰብስ ጥንቃቄ ማድረግ፣ ቆዳውን መሬት ላይ አለማድረቅ እና አለመገድገድ ጥንቃቄ የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት 27 ቢሊየን ጥሬ ቆዳና ሌጦ መመረቱን አስታውሰው÷ ከጥራት ጉድለት ጋር ተያይዞ ወደ ኢኮኖሚ የሚገባው ምርት ውስን እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ሕብረተሰቡ የጥንቃቄ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ ከቆዳ እና ሌጦ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በአድማሱ አራጋው