ሀጫሉ ሁንዴሳ ከመቃብር በላይ …
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀጫሉ ሁንዴሳ የህዝብ የችግር ቀን አለኝታ እና ድምፅ በመሆን ያሳረፈው አሻራ ስሙ በትውልድ ልብ ውስጥ ህያው እንዲሆን አስችሎታል።
ከአባቱ ሁንዴሳ ቦንሳና ከእናቱ ጉደቱ ሆራ በ1976 ዓ.ም በአምቦ ከተማ የተወለደው ሀጫሉ ሁንዴሳ፤ በቤተክርስቲያን ትምህርት የታነፀ እና ጥበብ በልጅነቱ ጠርታው ውድ የህዝብ ልጅ እንዲሆን ያስቻለውን አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ከልጅነቱ ጀምሮ ለህዝብ ባለው መቆርቆር እንዲሁም ለነጻነት፣ እኩልነት እና ፍትሃዊነት ቀናኢ ፍላጎት የተነሳ በ17 ዓመቱ በፖለቲካ ተሳትፎ ተጠርጥሮ ለአምስት ዓመታት በእስር አሳልፏል፡፡
በለጋ ዕድሜው ለዓመታት በእስር መቆየቱ የሀጫሉን ስነ-ልቦና ይበልጥ አጠንክሮት ‘ሰኚ ሞቲ’ የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሙን ዜማዎች በዚያው በመከራ ስፍራ ለማጠናቀቅ አስችሎታል፡፡
ሀጫሉ በሙዚቃ ስራዎቹ የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ፣ ማንነትና ጥያቄዎች በልዩ ጥበብ በማቅረብ ቀዳሚ የነበረ ሲሆን፤ ከስራዎቹ ዋኤ ኬኛ እና ማላን ጂራ የተሰኙት ስራዎቹ የሕዝቡን የልብ ትርታ በማስተጋባት የለውጥ መዝሙር ሆነው አገልግለዋል።
ሀጫሉ በሙዚቃ ስራዎቹ የትውልዱን የነፃነት ጥም በመግለጽና ሕዝባዊ ንቅናቄውን በማቀጣጠል ወደር የለሽ ድምጻዊ በመሆን ፋና ወጊ ነበር፡፡
በሙዚቃዎቹ ለተበደሉ ድምፅ፣ ለደከሙ ጉልበት እንዲሁም ተስፋ ላጡ የተስፋ ብርሃን በማሳየት የጥበብ ተሰጥኦውን ተጠቅሟል፡፡
ሀጫሉ የጥበብን ኃይል ለመብትና ለእኩልነት ትግል መሳሪያ በማድረግ በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ የማይፋቅ አሻራ ጥሎ አልፏል።
በመድረክ ላይ ያለው ወኔ፣ የቃላት ምርጫውና የዜማዎቹ ጥልቀት የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክና ወቅታዊ ጥያቄ ከማስተጋባት ባለፈ፣ ብዙዎችን ለለውጥ እንዲነሱ አነሳስቷል።
ሀጫሉ ለጥበብ ብቻ ሳይሆን ለቆመለት ዓላማ የታመነ፣ ደግና ሩኅሩኅ፣ ለሕዝብ ታላቅ ፍቅር ያለው ሞቱም ለትወልዱ የምንጊዜም ሀዘን ጥሎ አልፏል፡፡
የሀጫሉ የሙዚቃ ስራዎች ዛሬም ድረስ ተወዳጅነታቸው የማይደበዝዝና ሁሌም በከፍታ የሚሰሙ ናቸው፡፡
ከመቃብር በላይ ከፍ ብሎ የሚኖረው የሀጫሉ ሁንዴሳ ስም የኦሮሞ ሕዝብ የማንነት ተምሳሌትና የሰላማዊ ትግል ድምፅ ሆኖ ለዘላለም በታሪክ መዝገብ ላይ በደማቁ ተጽፎ ይኖራል።
አዲስ አበባ ከተማም ይህንን የህዝብ ልጅ ለመዘከር እና ለህያው ስራዎቹ መታሰቢያ በአፍሪካ ፓርክ የመታሰቢያ ሐውልት ገንብታ ይፋ አድርጋለች።
በአቤል ነዋይ