Fana: At a Speed of Life!

የለውጡ ጉዞና ተስፋ…

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት 8 ዓመታት የተጓዘችበት የለውጥ መስመር ተደቅኖባት ከነበሩ የህልውና አደጋዎች የታደገና ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያሸጋግር የታሪክ ድልድይ ነው።

በጊዜው ኢትዮጵያ በከፍተኛ የፖለቲካ ስብራት፣ በዴሞክራሲ ምህዳር መጥበብ እና በፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ጥያቄዎች ተወጥራ እንዲሁም ለሦስት አስርት ዓመታት በተዘራው የልዩነት እና የመከፋፈል ትርክት ለከፋ ችግር ተዳርጋ ነበር።

በተጨማሪም ለዘመናት ታምቀው የዘለቁ የማንነት፣ የወሰን እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ኢትዮጵያን ወደለየለት ቀውስ ውስጥ ሊከቷት የሚችሉበት ሁኔታ ነበር።

ነገር ግን በወቅቱ የለውጡ መንግስት በአብዮታዊ ጥፋት ሳይሆን ነባር ችግሮችን በመለየትና ተቋማትን በማሻሻል ላይ ያተኮረ ሪፎርም እንደ ብቸኛ መውጫ መንገድ በመምረጥ ሊከሰት የሚችለውን ውድመት ከማስቀረት ባለፈ የፌዴራል ስርዓቱ እንዲቀጥል ማድረግ ተችሏል።

እንዲሁም የለውጡ ኃይል የርዕዮተ ዓለም እስረኛ ከመሆን ይልቅ ለኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሚጠቅሙ እሳቤዎችን በማቀናጀት “የመደመር” መርህን የተከተለ ሲሆን÷ ይህም የጠላትነት ፖለቲካ ተወግዶ ተፎካካሪነት እንዲነግስ አድርጓል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተው ለውጡ በዳርና በመሃል፣ በአርሶና አርብቶ አደር መካከል የነበሩ የልዩነት ግንቦችን በማፍረስ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን÷ በተለይም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በስንዴ ልማትና በአረንጓዴ አሻራ የታየው ውጤት የሚደነቅ ነው።

በተጨማሪም ተቋማትን በማጠናከር እና በመገንባት ብሎም የመግባባት ዴሞክራሲ እንዲኖር ለማስቻል የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በመንግስሥ ከፍተኛ የስልጣን እርከን እንዲካተቱ መደረጉ አካታች እና አሳታፊ የሆነ የዴሞክራሲ ባሕል ለማሳደግ የተሰራውን ጥረት የሚያሳይ ነው።

ከዚህም ባሻገር መንግሥት የኑሮ ውድነት፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች እና የሰላም እጦትን ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ ሲሆን÷ በተለይም ፈተናዎችን በብሔራዊ ምክክርና በተቋማዊ ርምጃዎች ለመፍታት ያለው ቁርጠኛነት ትልቅ ዋጋ አለው።

ኢትዮጵያን ወደ ላቀ የከፍታ ማማ በማውጣት የታሪክ አሻራ ለማሳረፍ እና ለትውልድ የምትሻገር የበለጸገች ሀገር ለመገንባት እየተሰሩ የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎችን ማስቀጠል አስፈላጊ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.