Fana: At a Speed of Life!

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መራጮች ድምጽ እየሰጡ ነው – ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ እየተካሄደ በሚገኘው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መራጮች ድምጽ በመስጠት ላይ ናቸው አሉ።
የቦርድ ሰብሳቢዋ የምርጫውን ጊዜያው ሂደት በተመለከተ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷ ለምርጫው ስኬታማነት ወሳኝ የሆነው የቁሳቁስ ስርጭት ትናንት ምሽት 12 ሰዓት ላይ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቅቋል።
በ39 ሺህ 723 የምርጫ ጣቢያዎች ገለልተኛ ታዛቢዎች የምርጫ ሂደቱን እየተከታተሉ እንደሚገኙ አንስተዋል።
41 ሺህ 978 በሚሆኑት ጣቢያዎች ላይ ደግሞ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
ዲጂታል ምዝገባ በተደረገባቸው አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎችም ምርጫ ጣቢያዎች ረጃጅም ሰልፎች እየታዩ እንደሆነ የቦርድ ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።
በዲጂታል መንገድ በሞባይል አፕሊኬሽን፣ በዌብ ሳይት ወይም በቦርዱ ታብሌት የተመዘገቡ መራጮች ቅደም ተከተል በራሱ በሲስተሙ የሚወሰን መሆኑ ለረጅም ሰልፉ መፈጠር ምክንያት እንደሆነ ጠቁመዋል።
የመራጮች መዝገብ በአማርኛ አልፋቤት (ፊደል ተራ) ተከታትሎ ፕሪንት ሲደረግ አስቀድሞ የተሰጠ የገጽ ቁጥር ስለማይኖረው የተፈጠረ ችግር መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
ችግሩን በፍጥነት ለመፍታት በአሁኑ ወቅት መስመር ላይ ሰልፍ የያዙትን ተመዝጋቢዎች ዳታ ይዞ በማጣራት፣ ስንተኛው ገጽ ላይ እንደሚገኙ በካርዳቸው ጀርባ ላይ እየጻፉ በመስጠት መራጮችን በፍጥነት ማስተናገድ የሚቻልበት መንገድ እየተመቻቸ ይገኛል ብለዋል።
በሶስና አለማየሁ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.