ኢትዮጵያውያን የሰለጠነ ዴሞክራሲ አራማጆች መሆናቸውን ለዓለም አስመስክረዋል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያውያን የትኛውንም ልዩነት በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚችሉ የሰለጠነ ዴሞክራሲ አራማጆች መሆናቸውን ለዓለም አስመስክረዋል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ ኢትዮጵያውያን በታሪካችን አዲስ የድልና የከፍታ ምዕራፍ ፅፈናል ብለዋል።
ሕዝባችን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በነቂስ በመትመም ጠንካራና ሉዓላዊ ሀገረ መንግሥት ሊመሠረት የሚችለው በሕዝብ ነጻ ፍላጎትና በምርጫ ብቻ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል ነው ያሉት።
ከዚህ ታሪካዊ ሂደት የምንማረው ታላቅ እውነት አለ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም በሀገሪቱ የፖለቲካ ስልጣን ከሕዝብ ነጻ ድምፅ ውጪ በየትኛውም ሌላ አማራጭ በኃይልም ሆነ በጣልቃ ገብነት ሊመጣ እንደማይችልና እንደማይፈቀድ እንደሆነ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያውያን የትኛውንም ልዩነት በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚችሉ የሰለጠነ ዴሞክራሲ አራማጆች መሆናቸውን ለዓለም አስመስክረዋል ብለዋል።
እያንዳንዱ ዜጋ በብርድ፣ በቀትር ፀሐይ፣ በጨለማና ረጅም ሰዓታትን ተሰልፎ በመጠበቅ ሳይታክት በምርጫ ጣቢያ ተገኝቶ ድምፅ የሰጠው የሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ የመወሰን አቅም እንዳለው በጥልቅ ተረድቶ እንደሆነም ገልጸዋል።
ለዚህ ታሪካዊ ስኬት መገኘት ባለፉት ዓመታት የጀመርናቸው ተቋማዊ ሪፎርሞች ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋልም ነው ያሉት።
በተለይም በገለልተኝነትና በጥንካሬ የተገነቡ የዴሞክራሲ ተቋማት በሕዝባችን ዘንድ የፈጠሩት ከፍተኛ ቅቡልነትና እምነት ለዛሬው ስልጡን ሂደት ዋነኛ መሰረት ሆኗል ብለዋል።
በመጨረሻም ማረጋገጥ የምፈልገው የዚህ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት ምንም ይሁን ምን ኢትዮጵያ አሸንፋለች በማለት ገልጸው÷ የኢትዮጵያን መፍረስና መበታተን ሲመኙ የነበሩ፣ በምርጫው ሰበብ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ሌሊትና ቀን ያሴሩ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ፍላጎትና እኩይ ዕቅድ ሙሉ በሙሉ መክሸፉን አስረድተዋል።
የሀገራችንን አንድነትና ህልውና አስከብራችሁ፣ በነጻነት ድምፃችሁን ለሰጣችሁ ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁም ነው ያሉት በመልዕክታቸው።