Fana: At a Speed of Life!

ከአካባቢ ጥበቃ ወደ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና …

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የአየር ንብረት ለውጥን ጫና ለመቋቋም እና ዘላቂ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በዓለም አቀፍ ደረጃ አርአያ የሚሆኑ ተጨባጭ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች።

የሀገሪቱ የልማት አቅጣጫ የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠበቅ አልፎ የዜጎችን ኢኮኖሚ ከማሳደግና የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር ሁለንተናዊ ፋይዳ እያበረከተ ይገኛል።

ይህ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ በዋናነት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ በተፋሰስ ልማት እና በታዳሽ ኃይል ላይ በተመሰረተ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ዙሪያ ያጠነጥናል።

በኢትዮጵያ የደን ልማት ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ 48 ቢሊየን በላይ ችግኞች እንዲተከሉ ማድረግ ተችሏል።

ይህ ሰፊ ንቅናቄ የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከነበረበት የ11 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጓል።

የተተከሉ ችግኞች በአማካይ የጽድቀት መጠን 82 በመቶ መሆኑ ለሥራው ጥራትና ለሕዝቡ የነቃ ተሳትፎ ትልቅ ማሳያ ነው።

ዘንድሮም ይህ አበረታች ጉዞ ተጠናክሮ ሲቀጥል 9 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል የታቀደ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት ለደን ልማት የሚውሉ ሀገር በቀል ችግኞች ናቸው።

ቀሪው 60 በመቶ ደግሞ ለምግብነት እና ለሌሎች ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ዝርያዎች ሲሆኑ፤ ሥነ ምህዳርን ከመጠበቅ ባሻገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና የአርሶ አደሮችን ገቢ ለማሳደግ ወሳኝ ሚና አላቸው።

ከአካባቢ ጥበቃ ወሰን አልፎ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥን እያመጣ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ አንስቶ ሴቶችን በስፋት ማሳተፍን ጨምሮ ከ1 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯል።

በተጎዱ መሬቶች ላይ የተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የአፈር መሸርሸርን ከመከላከል ባለፈ፣ የውሃ ሀብትን በማቆርና የብዝኃ ሕይወትን መልሶ በማነቃቃት አካባቢዎችን ለቱሪዝም መስህብነት እያበቁት ይገኛሉ።

ከደን ልማት ጎን ለጎን ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በምታደርገው ጥረት፣ የትራንስፖርት ዘርፉን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለመተካት እየወሰደች ያለው ርምጃ ተስፋ ሰጪ ነው።

ሀገሪቱ ከ90 በመቶ በላይ የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ከንጹህ የውሃ ሀብት በመሆኑ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ሲሆን በፈረንጆቹ 2030 በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር 400 ሺህ ለማድረስ የተቀመጠው ግብ፣ ለሌሎች ሀገራት አብነት የሚሆን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጉዞ አካል ነው።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እና በዘላቂ የልማት ፖሊሲዎቿ አማካኝነት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆናለች።

ይህ ሁሉ የተቀናጀ ጥረት ኢትዮጵያ ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴ፣ ቀልጣፋ እና የበለፀገች ሀገርን ለማስረከብ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ ነው።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.