ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን ለማጠናከር…
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን ለማሳደግ የምታከናውናቸውን ተግባራት አጠናክራ ትቀጥላለች አሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ (ኢ/ር)።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል ልማት በትኩረት እየሰራች ትገኛለች።
ባለፉት ዓመታት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሶስት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ገልጸው÷ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት በስፋት መስራቷ በዘርፉ ተጠቃሽ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን አስችሏል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ በሙሉ ከታዳሽና ንፁህ ኃይል የሚገኝ መሆኑንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር ተቋም ውስጥ በግንባር ቀደምነት እየሰራች መሆኗን አንስተው÷ ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን ለማጎልበት የምታከናውነውን ተግባር አጠናክራ መቀጠሏን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ኃይል ከምታቀርብላቸው ከጅቡቲ፣ ሱዳንና ኬንያ በተጨማሪ ወደ ታንዛኒያ የኃይል ሽያጭ ሙከራ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው÷ ከሌሎች ሀገራት ጋርም በኃይል ለመተሳሰር ጥናት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለውጭ ሀገራት የምታቀርበው ከምታመነጨው ኃይል አስር በመቶ ያነሰ እንደሆነ በመግለጽ÷ የሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት የምታቀርበውን ኃይል በማቀናጀት በታዳሽ ኃይል ቀዳሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ግዙፍ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ በፍጥነት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
16 የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ፕሮጀክቶችም በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው÷ ተቋሙ የኢትዮጵያን ልማትና ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።