4 ሚሊየን አዲስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ እየታተመ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለያዩ የደህንነት መስፈርቶችን ያሟላ 4 ሚሊየን አዲስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ እየታተመ ነው አለ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዛሬ ጀምሮ አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ መሰጠት ጀምሯል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አሰፋ ሀዲስ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳስታወቁት ÷ የተሽከርካሪ ሰሌዳው ወጥ፣ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ያከበረ እና አመሳስሎ ለመስራት ተጋላጭ ያልሆነ ነው።
የተሽከርካሪ ሰሌዳው ዋጋ እንደ ተሽከርካሪው አይነት የሚለያይ መሆኑን ጠቁመው÷ የሰሌዳ ዋጋው የአገልግሎት ዘመኑን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
በግለሰብ፣ በብዙሃን ትራንስፖርት እና በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መካከል ያለው የሰሌዳ ዋጋ የተለያየ መሆኑንም አንስተዋል።
አማካሪው እንዳሉት÷ ለኤሌክትሪክ እና ለብዙሃን ትራንስፖርት የሰሌዳ ዋጋ ድጎማ ይደረግለታል።
ይህ ሰሌዳ “ኪው አር ኮድ”፣ ማይክሮ ችፕስ እና ሌሎች የደህንነት መስፈርቶችን እንዲሁም የግለሰቦችን የሰሌዳ ፍላጎት ያሟላ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አሁን ላይ 800ሺህ ተሽከርካሪዎች ሲስተም ላይ ተመዝግበው እንደሚገኙም ተናግረዋል።
በመሳፍንት እያዩ