Fana: At a Speed of Life!

መዋቅራዊ ስብራቶችን ለመጠገን ምን ይቀነስ?

የዜጎችን ተጠቃሚነትና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የመቀነስ ግቦች አስፈላጊ ናቸው፡፡

ይህ የመቀነስ ስትራቴጂ ከዜሮ ግቦች ጎን ለጎን የተቀረጸ ሲሆን፣ ዓላማውም ድህነትንና ጉስቁልናን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስና ማክሰም ነው። እነዚህ ግቦች ወደ መሬት ወርደው ህዝባዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራባቸው ይገኛል።

በዚሁ መሠረት ኢትዮጵያ ከራሷ ላይ ለመቀነስ የያዘቻቸው ግቦች፡-

  1. ኑሮ ውድነትን መቀነስ

የኑሮ ውድነት የዜጎችን የእለት ተእለት ህይወት የሚፈትሽ ቀዳሚ ማህበራዊ አደጋ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የምርት አቅርቦትን ማሳደግ ላይ አተኩሯል። በተለይም በከተማ ግብርና፣ በኩታ ገጠም የሽንኩርትና የአትክልት ልማት እንዲሁም በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር አማካኝነት የምግብ ምርቶችን በቀጥታ ለተጠቃሚው በማድረስ የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል።

  1. ሌብነትን (ሙስናን) መቀነስ

የህዝብንና የሀገርን ሀብት ለግል ጥቅም ማዋል የልማት ቀዳሚ ጠላት ነው። የሌብነትና የብልሹ አሰራርን ሰንሰለት ለመስበር ተቋማዊ ሪፎርሞችን ማካሄድ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማዘመንና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ዋነኞቹ መፍትሄዎች ተደርገው ተወስደዋል። ዓላማው ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል የሰፈነባት ኢትዮጵያን መገንባት ነው።

  1. መንደርተኝነትንና ጎጠኝነትን መቀነስ

ዋልታ ረገጥና ጽንፈኝነት፣ የጎሳ ፖለቲካ እና የመንደርተኝነት አስተሳሰብ የሀገርን አንድነትና የህዝብን ነፃ እንቅስቃሴ የሚገድቡ ስብራቶች ናቸው። ይህንን በመቀነስ፣ ሁሉንም ዜጋ እኩል የሚያስተናግድ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትንና የመደመር እሳቤን በተግባር ማጽናት የዚህ ግብ ዋነኛ መርህ ነው። ዜጎች በማንነታቸው ሳይገደቡ በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል ሰርተው እንዲበለፅጉ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ላይ ያተኩራል።

  1. ጠባቂነትን መነስ

ከመንግሥት ወይም ከውጭ እርዳታ እጅ መጠበቅ የአንድን ህዝብ የስራ ባህልና የፈጠራ አቅም ያኮስሳል። ይህንን ጎጂ የጥገኝነት ስነ-ልቦናና አስተሳሰብ በመቀነስ፣ እያንዳንዱ ዜጋ በራሱ ጉልበትና እውቀት ሰርቶ እንዲለወጥ የስራ ባህልን ማነቃቃትና የስራ ዕድል ፈጠራን ማስፋፋት የስትራቴጂው አካል ነው።

  1. ለኑሮ የማይመቹ ቤቶችን መቀነስ

ይህ ግብ የዜጎችን የመኖሪያና የህይወት ደረጃ ከማሻሻል ጋር የተያያዘ ነው። በከተሞችም ሆነ በገጠር የሚገኙ ያረጁና የተጎሳቆሉ ቤቶችን ደረጃ በደረጃ በመቀነስ፣ በምትካቸው ዘመናዊ፣ ፅዱ እና ለኑሮ ምቹ የሆኑ የኮሪደር ልማትና የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት የህዝብን ክብርና የእኗኗር ዘይቤ ማሳደግን ያለመ ነው።

በአጠቃላይ የመደመር መንግሥት የመቀነስ ግቦች ስኬት የሚለካው እነዚህ አምስቱ ክስተቶች ከዜጎች ትከሻ ላይ ሲወርዱ ነው። ይህንን ለማሳካት የአመራሩ ቁርጠኝነት፣ የህዝብ ንቁ ተሳትፎና የፖሊሲዎች በአግባቡ መተግበር ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

እኛም በእዚህ ውስጥ ሚናችንን ብንወጣ ነገ ታሪክ በበጎ ያስበናል!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.