ለቀጣናው ዋስትና እየሆነች ያለች ሀገር
የኢትዮጵያ የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት ዘመናዊ ቴክኖሎጂንና ሰብአዊ አቅምን በማስተባበር በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን የጎላ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት እና በፌደራል ፖሊስ የተገነባው ይህ አስተማማኝ አቅም ቀጣናዊ የሽብር አደጋዎችን እና ሕገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውርን በመከላከል ረገድ ለአፍሪካ ቀንድ የማይተካ የደኅንነት ዋስትና ሆኗል።
የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጡ፣ በተለዋዋጭ የደኅንነት ምኅዳር እና በተለያዩ የድንበር ተሻጋሪ አደጋዎች የተከበበ ነው።
በእነዚህ ፈተናዎች መካከል ኢትዮጵያ ታሪካዊ ክብሯን እና የሕዝቦቿን ሰላም ለማስጠበቅ የገነባቻቸው የደኅንነትና የፀጥታ ተቋማት፤ በማንኛውም ዓይነት የውስጥም ሆነ የውጭ ሤራ የማትበገር ጽኑ ሀገር መሆኗን በተግባር እያሳዩ ይገኛሉ።
ተቋማቱ በሰው ኃይልና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አቅም በመገንባታቸው ተልዕኳቸውን በብቃት እየተወጡ ይገኛሉ።
ባለፉት ሀገራዊ የለውጥ ዓመታት ውስጥ መንግሥት ከተገበራቸው የሪፎርም አምዶች አንዱ ጠንካራና ገለልተኛ የፀጥታና የደኅንነት ተቋማትን መገንባት ነበር።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት በቴክኖሎጂ፣ በመረጃና በሳይበር ሥርዓት የዘመነ አቅም በመገንባት ላይ ይገኛል።
ሰራዊቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ያተረፈ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ለቀጣናው ሀገራት መከታና የሰላም ምሰሶ አድርጓታል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በበኩሉ የቀጣናውን የፀጥታ ሁኔታ በጥልቀት በመተንተን አሸባሪ ቡድኖችና አደገኛ አውታረ መረቦችን ቀድሞ በመምታት ሀገራዊና ቀጣናዊ ሰላምን በማስጠበቅ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስልታዊ ድሮኖችን በመታጠቅ የአየር ክልሉን ፍፁም የማይደፈር አድርጎታል።
የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ደግሞ ኢትዮጵያ በግፍ ወደ ተነጠቀችው የባህር በር ለመመለስና የኢትዮጵያን የወደፊት የኢኮኖሚና የደኅንነት ጥቅም ለመጠበቅ በንቃት ራሱን አደራጅቶ ለተልእኮ እየተዘጋጀ ይገኛል።
በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ ለዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች፣ ለሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያና የሰዎች ዝውውር ተጋላጭ ነው።
የኢትዮጵያ የፀጥታ ተቋማት መረጃዎችን በወቅቱ በመለዋወጥ እና በማክሸፍ በቀጣናው ላይ ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን አስቀርተዋል።
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ አሰራሮች ምንም ዓይነት የስጋት ደረጃ እንደሌለባቸው የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ያረጋገጠው፣ ተቋማቱ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውን አሳይቷል።
አዳዲስ ጦርነቶች በሳይበር ሥርዓት እና በፈጣን መረጃ ልውውጥ ላይ በተመሰረቱበት በዚህ ዘመን፣ የሀገሪቱ የሳይበር ደኅንነት ተቋማት ሀገራዊና ቀጣናዊ መሠረተ ልማቶችን ከአደጋ በመጠበቅ አስተማማኝ ዋስትና ሆነዋል።
የኢትዮጵያ የደኅንነትና የፀጥታ ተቋማት ሁለንተናዊ አቅም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ሰላምና ልማት ከማረጋገጥ ባለፈ ለቀጣናው አፍሪካ ቀንድ የሰላምና መረጋጋት ትልቅ ዋስትና ናቸው።
ተቋማቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል እና በብቃት በመታገዛቸው ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የፖለቲካና የደኅንነት አጋርነት አጠናክረው የሚያስቀጥሉ ናቸው፡፡