Fana: At a Speed of Life!

ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ – ለዓመታት ያካበቱትን ልምድ ተጠቅመው ለአፍሪካ ሰላም እየሰሩ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ዘንድ በእጅጉ ይታወቃሉ።

ኦባሳንጆ በሀገራቸው ናይጄሪያ እንዲሁም በአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት ሰላም ይሰፍን ዘንድ የግል ተሞክሯቸውን፣ የህይወት ልምድና ያለፉበትን ታሪክ መሰረት አድርገው ብዙ ሰርተዋል። አሁንም እየሰሩ ይገኛል።

“ለአህጉራዊ ችግሮች አህጉራዊ መፍትሄ” የሚለው መርህ የአፍሪካ ሀገራት የወል ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ከአህጉሪቷ ውጪ ካሉ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ነፃ በሆነ መልኩ በራሳቸው አቅም፣ እውቀት እና አህጉራዊ ተቋማት አሸማጋይነት፤ ለምሳሌ እንደ አፍሪካ ህብረት ባሉ ተቋሞቻቸው እንዲፈቱ የሚያስችል ፓን-አፍሪካዊ እሳቤ ነው።

በዚህ እሳቤም በተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የውስጥም ሆነ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፡፡

በዚህ እሳቤ በጽኑ የሚያምኑት ኦባሳንጆ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሃት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት እውን እንዲሆን አሻራቸውን አኑረዋል።

የዚህን ስምምነት አፍሪካዊ መርህና በስኬት የተረጋገጠባቸውን ዋና ዋና ነጥቦችን ስንመለከት፤ የመጀመሪያው የሰላም ድርድሩ ሙሉ በሙሉ የተመራው እና የተቀናጀው በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት ነው።

የውጭ ኃይሎች በሂደቱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እና የራሳቸውን ፍላጎት ለመጫን ቢሞክሩም፣ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ስር ባሉ ታዋቂ የአፍሪካ መሪዎች በዋናነት በነ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አስተባባሪነት እንዲመራ ተደርጓል።

ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ “በአፍሪካ ውስጥ ሊፈታ የማይችል እና ከአፍሪካውያን አቅም በላይ የሆነ ችግር የለም” የሚለው ንግግራቸው ለዚህ አፍሪካዊ መርህ ስኬት ያላቸውን ጽኑ አቋም ያሳያል፡፡
 
ኦባሳንጆ የአፍሪካን ውስብስብ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው በተለያዩ ወገኖች መካከል መተማመን እንዲፈጠር እና ስምምነት ላይ እንዲደረስ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።

አፍሪካውያን የራሳቸውን የቤት ስራ ራሳቸው መሥራት እንደሚችሉ በማሳየት፣ የውጭ ኃይሎች ሚና በአፍሪካ ህብረት መሪነት ስር ድጋፍ ከመስጠት እንዳይዘል በማድረግ መርሁ እንዲተገበር አስቻይ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የአፍሪካ ሀገሮች ባደረጉት ዘመናትን የወሰደና ብዙ መስዋዕትነትን ያስከፈለ ተጋድሎ ከቅኝ ገዥዎቻቸው መዳፍ ነጻ መውጣት ችለዋል፤ ይህን ድል በመቀዳጀትም በሀገራቸውና በአህጉራቸው እጣ ፈንታ ላይም መወሰን በሚያስችላቸው ማማ ላይ ተቀምጠዋል ይላሉ።

ልክ እንደ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ያሉ ቁርጠኛ የአፍሪካ መሪዎች እና እንደ አፍሪካ ህብረት ያሉ ጠንካራ ተቋማት ካሉ፤ የአህጉሪቱን ሰላምና መረጋጋት ያለ ውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት ማረጋገጥ እንደሚቻል ለዓለም ህዝብ ታላቅ ትምህርት ሰጥቶ አልፏል፡፡

አሁንም ኢትዮጵያ ለምታከናውነው ሀገራዊ ምክክር የኦባሳንጆ የሰላም ሂደትን የመምራት ልምድ ትልቅ ትምህርት ይዞ እንደሚመጣ አያጠራጥርም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ስለኦባሳንጆ ሲገልጹ፤ ከዚህ ቀደም ካከናወኗቸው ተግባራት ጥበብ መቅሰም ችለናል፤ በተለይም የቢያፍራን የሰላም ሂደት በመምራት ያካበቱትን ልምድ አጋርተውናል ይላሉ።

ይህም ኢትዮጵያ በምክክር ለምታረጋግጠው አንድነትና ዘላቂ የሰላም ጉዞ ትልቅ ትምህርት ይሰጣል፤ ኢትዮጵያም ኦባሳንጆ ለሚያበረክቱት በዋጋ የማይተመን አስተዋጽኦ ሁልጊዜም የላቀ ምስጋናዋን ታቀርባለች።

በመልካም ፈቃዱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.