Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለዘመናት የቆዩ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት የሀገርን ሰላም፣ አንድነት እና የጋራ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡

ለሦስት ሳምንታት የሚቆየው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በትናንትናው ዕለት ተጀምሯል፡፡

ለአህጉራዊ ችግሮች አህጉራዊ መፍትሄ በሚለው ፓን አፍሪካዊ መርህ የተቃኘው ይህ መድረክ አፍሪካዊ መፍትሄዎችን ለአፍሪካውያን እውን ለማድረግ በአህጉሪቱ ልጆች ይመራል፡፡

የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በትናንትናው ዕለት በተጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ በመገኘት የሰላም ውይይትን በመምራት ያካበቱትን ልምድ ለኢትዮጵያውያን አካፍለዋል፡፡

ኢትዮጵያና ናይጄሪያ ያሳለፉት የእርስ በእርስ የጦርነት ታሪክ እንደሚያመሳስላቸው አውስተው፤ በእርስ በእርስ ጦርነት አሸናፊም ተሸናፊም የለም ብለዋል፡፡

ናይጄሪያ ከአስከፊው የእርስ በእርስ ጦርነት የወጣችው በምክክር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሁሉን አሳታፊ የፖለቲካ ምክክር መድረኮች ስህተትን ለማረምና ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለመወሰን እድል እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን አድንቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ በበኩላቸው፤ ይህ ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ የዴሞከራሲ ግንባታ ሂደት እና ዘላቂ ሰላም ጥረት ትልቅ ማረጋገጫ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና በፖለቲካ ምህዳሩ ውስጥ መተማመንን ለመፍጠር ያግዛል ነው ያሉት፡፡

ሀገር በቀል የምክክር ሂደቶች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአህገሪቱ ምሳሌ እንደሚሆኑ በመገለጽ፤ መሰል ምክክሮች በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሊለመዱ ይገባል ብለዋል፡፡

ከሕብረቱ አጀንዳ 2063 ዕቅዶች አንዱ በአህጉሪቷ ሰላም ማረጋገጥ እንደሆነ አውስተው፤ የአፍሪካ ሕብረት ይህንን ታሪካዊ የምክክር ክስተት ሙሉ በሙሉ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የፓን አፍሪካኒዝም መሪ ሀገር ሆና መቆየቷን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የሁሉም አፍሪካውያን ሰላም እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ስኬት መላውን የአፍሪካ ቀንድ ወደ ብሩህ ተስፋ የሚመራ ርምጃ ነው ያሉት ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን መልስ ፍለጋ ወደ ውጭ ከመመልከት ይልቅ የሀገር በቀል የሽምግልና እና የእርቅ እሴቶቻቸውን በመጠቀም ወደ ውስጥ መመልከት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

በዚህም የሀገሪቱን ውስጣዊ ችግሮች ከመፍታት ባለፈ ለአፍሪካና ለመላው ዓለም ጭምር ምሳሌ የሚሆን መፍትሔ ማምጣት ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያውያን በብዕር ኃይል፣ በውይይትና በጋራ መከባበር ልዩነቶቻቸው መፍታት እንደሚችሉ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብና ለራሳቸው የሚያሳዩበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡

ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ ልዩነቶችን በሰለጠነ ሰላማዊ መንገድ በመፍታት ብሔራዊ መግባባትን የተጎናጸፈች፣ ጥቅሟ የተጠበቀ፣ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖዋ ጉልህ የሆነና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ ወሳኝ ርምጃ ነው፡፡

በመልካም ፈቃዱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.