Fana: At a Speed of Life!

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከ42 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በበጀት ዓመቱ ፓስፖርት እና ቪዛን ጨምሮ ከተለያዩ አገልግሎቶች ከ42 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰብስቤያለሁ አለ፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፥ በጀት ዓመቱ በአየርና በድንበር ለ7 ነጥብ 2 ሚሊየን ገቢና ወጪ መንገደኞች አገልግሎት ተሰጥቷል።

አገልግሎቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ፓስፖርት መስጠቱን ጠቅሰው፥ ተደራሽነቱን ለማስፋት የአገልግሎት መስጫ ቅርንጫፎችን ወደ 23 ማድረሱን ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ከ1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ የውጪ ሀገር ዜጎች አገልግሎት መሰጠቱን አንስተዋል።

ተቋሙ ፓስፖርትና ቪዛን ጨምሮ ከሰጣቸው አገልግሎቶች በአጠቃላይ ከ42 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

433 የውጭ ዜጎችና 4ሺህ 450 ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ 4ሺህ 883 ዜጎች በሐሰተኛ ሰነድ የማጭበርበር ድርጊት ሲፈጽሙ ተይዘው ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል ነው ያሉት።

በተጨማሪም 25ሺህ 407 ኢትዮጵያውያን እና 29ሺህ 606 የውጭ ሀገር ዜጎች በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ሊገቡና ሊወጡ ሲሉ ተይዘው ርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.