በበጀት ዓመቱ የተቋም ግንባታ፣ የዴሞክራሲ ስርዓትና የልማት ከፍታ ተረጋግጧል – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመቱ የተቋም ግንባታ፣ የዴሞክራሲ ስርዓትና የልማት ከፍታ የተረጋገጠበት ነው አሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ የውይይት መድረክ በአዲስአበባ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ም/ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የዋና ጽ/ቤት የዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የቅ/ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ሌሎች አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።
አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በበጀት ዓመቱ በተቋም ግንባታ፣ በዴሞክራሲ ሥርዓትና በልማት ሥራዎች ጉልህ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ በአደረጃጀት፣ በአሰራር፣ በሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት እንዲሁም በማስፈጸም አቅሙ ተጠናክሮ የወጣበት ዓመት መሆኑን ጠቅሰው፥ ድርብርብ ተልዕኮዎችን በታቀደው መሰረት ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
መላው ሕዝባችን በእያንዳንዱ ተልዕኮ ላይ በንቃት በማሳተፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ በመደረጉና በባለቤትነት ስሜት ከፓርቲያችን ጎን በመቆሙ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዟችን ጠንካራ መሠረት የጣለውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ መንታ ግቦች በላቀ አፈጻጸም ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
ልማትና ዴሞክራሲን ጎን ለጎን በማስኬድ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት የላቀ ውጤት መመዝቡን አስረድተዋል፡፡
የፓርቲውን ግዙፍ አቅም አሟጥጦ በመጠቀምና የአመራር ስነ ምግባር ልህቀትን በማረጋገጥ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአመራርና አባላትን አቅም ማጎልበትና የብሔራዊነት ገዥ ትርክትን ማስረጽን ጨምሮ በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በብቃት ለመፈጸም በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በተጠናከረ መንገድ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
ለዚህም የፓርቲው አመራር፣ አባላትና የመላው ሕዝብ ርብርብ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ ላይ በ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትና በ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ፓርቲው ገልጿል፡፡