ራሱን ጽምዶ በሚል የሚጠራውንና የጦርነት አባዜ የተጠናወተውን ቡድን ሁሉም ሊታገለው ይገባል – ግንባር ሕዝባዊ ማዕበል ብርጌድ ንሃመዱ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ራሱን ጽምዶ በሚል የሚጠራውንና ሕዝባዊ መሠረት የሌለውን ሕገ ወጥ ቡድን ሁሉም ሊታገለው ይገባል አለ ግንባር ሕዝባዊ ማዕበል ብርጌድ ንሃመዱ፡፡
የኤርትራን አምባገነን ሥርዓት ለመታገል የተቋቋመው ግንባር ሕዝባዊ ማዕበል ብርጌድ ንሃመዱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
ግንባር ሕዝባዊ ማዕበል ብርጌድ ንሃመዱ በመግለጫው ÷ ‘ጽምዶ’ በሚል ራሱን የሚጠራውን ሕገ ወጥ ቡድን እንቅስቃሴ ለቀጣናው ስጋት በመሆኑ ሁሉም አጥብቆ ሊቃወመውና ሊታገለው እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡
በኤርትራ ሕዝባዊ መሠረት ያለው መሆኑን ያስታወቀው ግንባሩ ÷ የጦርነት አባዜ የተጠናወተውን ጽምዶን እንደማይደግፍ እና ዋነኛ ዓላማውም የዚህን ቡድን የጥፋት መንገድ መከላከልና ማክሸፍ መሆኑን ገልጿል፡፡
የኤርትራ ሕዝብ በጦርነት ብዙ ዋጋ የከፈለ በመሆኑ ጦርነት እንደማይበጀው እና እንደማይፈልግ በመግለጽ ትኩረቱ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ላይ መሆኑን ጠቁሟል።
ሆኖም ጽምዶ የጦርነት ሀሳብን የሚያራምድ እና ቤተሰቦቻቸውን በግዳጅ እያፈሰ የሚወስድ ነው፤ ይህም ለትግራይ እና ለኤርትራ ሕዝብ አልፎም ለቀጣናው ትልቅ ስጋት ነው ብሏል።
በመሆኑም ሁሉም ወገን ይህንን ሕዝባዊ መሠረት የሌለው ቡድን በጋራ ሊታገለው እንደሚገባ ያሳሰበው ግንባሩ÷ በኤርትራ ስላለው የፖለቲካ እና ማህበራዊ ቀውስ ዙሪያም ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
ባለፉት 30 ዓመታት በስልጣን ላይ ባለው አምባገነን መንግሥት ምክንያት ኤርትራውያን በርካታ ፈተናዎችን እንዳሳለፉና ሀገር እያላቸው ሀገር እንደሌለው ዜጋ እንዲኖሩ መፈረዱን አስረድቷል።
በአምባገነኑ ሥርዓት ምክንያት ዜጎች በከፋ ድህነት ውስጥ እንዲኖሩ መደረጉን ተከትሎ በርካቶች ሀገራቸውን ጥለው ወደ ተለያዩ ሀገራት ተሰደው ለመኖር መገደዳቸውን ነው መግለጫው ያመላከተው፡፡
ግንባር ሕዝባዊ ማዕበል ብርጌድ ንሃመዱ የተመሠረተው ይህንን የሕዝብ ሰቆቃ ለመቀልበስ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷ ዋነኛ ዓላማው አምባገነኑን ሥርዓት ታግሎ በመጣል ሕዝባዊ መንግሥት መመሥረት መሆኑን አብራርቷል።
ሀገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሻገር ጽኑ ትግል እንደሚያደርግ ያወሳው ግንባሩ ÷ኤርትራ ከጎረቤቶቿ ጋር እንዳትገናኝ ተደርጋ የቆየችበትን ዝግ አሠራር ሰብሮ በማውጣት ትስስሯን ወደሚያጠናክርበት ምዕራፍ ለማሸጋገር ጠንክሮ እንደሚሰራ አስታውቋል።
በዓለምሰገድ አሳዬ