መደመር በሕዝብ ስም የሚደረግ የለቅሶ ፖለቲካን ያስቀረ እሳቤ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤምሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መደመር በሕዝብ ትግል ስም የሚደረግ የለቅሶ ፖለቲካን ያስቀረ እሳቤ ነው አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ጋር ባደረጉት ቆይታ የመደመር እሳቤ በሁሉም ዘርፎች ለተመዘገቡ ተጨባጭ ስኬቶች መሰረት የሆነ ሀገር በቀል እሳቤ ነው ብለዋል።
በህዝብ ትግል ስም የኦሮሞን ህዝብ ወደ ብሶት ለመክተት ከንቱ ጥረት የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን በማንሳት መደመር በሕዝብ ትግል ስም የሚደረግ የለቅሶ ፖለቲካ ያስቀረ እሳቤ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እውነተኛ የፖለቲካ መሪ ዋና ተግባር ህዝብን ከገባበት ችግርና መከራ አውጥቶ ወደ በጎና የተሻለ ህይወት ማሸጋገር ነው ሲሉም አመልክተዋል።
የኢኮኖሚ ሪፎርም በተመለከተ በኦሮሚያ ክልል በመስኖ ልማት ትልልቅ ስራዎች ተሰርተዋል ብለው ለዚህም በቦረናና በባሌ ዞኖች የተመዘገበው ውጤት ጥሩ ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በመደመር እሳቤ በውጭ ጉዳይ ዘርፍ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነትና ገጽታ ያሳደጉ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
የመደመር ሀሳብ የያዘው መጽሐፍ በ10 የተለያዩ ቋንቋዎች መተርጎሙንና ሀሳቡ በተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ማየት መቻሉን ተናግረዋል።