Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ቀጣናዊ የጤና ጉባኤ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያለፈችበትን ጉዞ ለማሳየት ዕድል ይፈጥራል – ዶ/ር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15/2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ጉባኤ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያለፈችበትን ረጅም ጉዞ ለማሳየት ዕድል የሚፈጥር ነው አሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፡፡

ኢትዮጵያ 76ኛውን የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ኮሚቴ ስብሰባ በሚቀጥለው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ ታስተናግዳለች።

ሚኒስትሯ ጉባኤውን አስመልክተው ከድርጅቱ የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ፕ/ር መሐመድ ጃናቢ ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ጉባኤውን ማስተናገድ ለኢትዮጵያ ትልቅ ክብርና ደስታ ነው ብለዋል።

ሁነቱ ዓለም አቀፍ ስብሰባን ከማስተናገድ በላይ ትርጉም እንዳለው ገልጸው፥ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያለፈችበትን ረጅም ጉዞ ለማሳየት እንዲሁም ልምድና ራዕይዋን ለአፍሪካ የጋራ ጥረት ለማበርከት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ጉባኤውን ስታስተናግድ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅሰው፤ ይህም በየጊዜው በዘርፉ እያሳየች ያለችውን እድገት የሚያንፀባርቅ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በተለይም ከ5 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት፣ የጨቅላ ሕፃናትና የእናቶች ሞት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን አብራርተዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.