የአገልግሎትና የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ነው – ሽሻይ አማረ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአገልግሎትና የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ነው አሉ የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሽሻይ አማረ(ዶ/ር)።
የከተማዋ ከንቲባ ሽሻይ አማረ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተዘዋውረው ባደረጉት የመስክ ምልከታ ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት መፈጸሙን መታዘባቸውን ገልጸው፣ የተስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት አጣዳፊ ምላሽ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም መሰረት በእለት ጉርስ እጥረት ለተጎዱ ህጻናት፣ እናቶችና አረጋውያን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ማዳረስ ቀዳሚ ተግባር ተደርጎ እየተሰራበት ይገኛል ነው ያሉት።
በተጨማሪም የተቋረጠውን የማስተማር ሂደት ለማስጀመርና ትምህርት ቤቶች በፍጥነት በራቸውን ከፍተው ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ ስራ ያላቆሙ የጤና ተቋማት አቅማቸው ተጠናክሮ ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ሲሉ አመልክተዋል።
ከነዚህ የማገገም ስራዎች ጎን ለጎን የባለአደራ አስተዳደሩ ከተሰጡት አጣዳፊ ስራዎች ባሻገር በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ የትግራይ ህዝብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመረጠው አካል እንዲመራ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የመፍጠርና አሰራር የመዘርጋት ተልዕኮውን እንደሚያሳካ ከንቲባው አብራርተዋል።
ህዝቡ ከህገ-ወጡ የህወሓት አገዛዝ ነፃ በመውጣቱ ያገኘውን ሰላምና እረፍት አሳልፎ እንደማይሰጥ የጠቆሙት ከንቲባው የፌደራል መንግሥት በፀጥታ ማፅናትና በሰላም ማስከበር ሂደቱ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ህዝቡም ለልማት ከባለአደራ አስተዳደሩ ጎን እንደሚቆም ማረጋገጡን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት መቐለ ከተማ በጥሩ የማገገምና የመነቃቃት ሁኔታ ላይ እንደምትገኝም ጠቁመዋል።
በእመቤት ሲሳይ