Fana: At a Speed of Life!

ሳትነሳ የወደቀችው ኤርትራ – “የአፍሪካዋ ሲንጋፖር” ምፀት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኤርትራ በ1983 ነፃነቷን ስታወጅና በ1985 በይፋ ስትመሰረት፣ በብዙዎች ዘንድ በአፍሪካ ቀንድ የዲሞክራሲና የኢኮኖሚ ዓብነት ትሆናለች የሚል ግምት ነበር።

በምዕራባውያን ዘንድ የሀገሪቱ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ከፖል ካጋሚ እና መለስ ዜናዊ ጋር “አዲሶቹ የአፍሪካ መሪዎች“ ተብለው የተወደሱ እና በአህጉሪቱ ዴሞክራሲንና ልማትን ያመጣሉ ተብለው እምነት የተጣለባቸው ፖለቲከኞች ነበሩ፡፡

የኤርትራው መሪ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራ እንደ ሀገር በተመሰረተችበት ወቅት ሀገሪቱን የላቀ የንግድ ማዕከልና በኢኮኖሚ ብልጽግና “የአፍሪካዋ ሲንጋፖር” እንደሚያደርጓት ቃል ገብተው ነበር።

ሆኖም ባለፉት 35 ዓመታት ቃላቸውን ቅርጥፍ አድርገው የበሉ ሲሆን የተመዘገበው ውጤት ከገቡት ቃል ፍፁም ተቃራኒ ሆኗል።

የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከባድ ውድቀቶች ከገጠማቸው የቀጣናው ሀገራት ውስጥ ቀዳሚ መሆኑን የተለያዩ ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት ሪፖርቶች ያመላክታሉ።

ሀገሪቱ በግል ድርጅቶችና በውጭ ኢንቨስትመንት ላይ የጣለችው ጥብቅ ገደብ፣ የባንክ ሥርዓቱ እንዲዳከም እና ወጣቱ አምራች ኃይል በግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት መጠመዱ ኢኮኖሚዋ እንዲሽመደመድ አድርጎታል።

ኤርትራ ሕገ-መንግሥት የሌላት፣ ነፃ ገለልተኛ ፍርድ ቤትና የፓርላማ ሥርዓት የሌላት የአንድ አምባገነን መሪ የግል ንብረት ሆና ቀርታለች። ኤርትራውያንን ነጻ አወጣለሁ ብሎ ስልጣን የተቆናጠጠው ሻዕቢያ፣ በብሔራዊ አገልግሎት፣ በአፈና እና በጭቆና ወጣቱን ለስደት በመዳረግ ሀገሪቱን አምራች ኃይል የለሽ አድርጓታል፡፡

በኤርትራ ብቸኛው ጠንካራ ተቋም ቢኖር ወታደራዊ እና የጸጥታ ተቋማት ብቻ ሲሆኑ በጥንካሬ መዝለቃቸው ከአዛውንቱ ፕሬዚዳንት ህልውና ጋር የተሳሰሩ በመሆናቸው ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በተደጋጋሚ ባወጣቸው ሪፖርቶች፣ በሀገሪቱ ውስጥ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች “በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች” ደረጃ የሚመደቡ መሆናቸውን አስታውቋል። የፖለቲካ ተቃዋሚዎች፣ ነፃ ጋዜጠኞችና የሃይማኖት መሪዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማይታወቁ እስር ቤቶች እየማቀቁ ነው፡፡

አገዛዙ በዲፕሎማሲው ረገድም ሀገሪቱ ለረጅም ዓመታት በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የተገለለችና ከጎረቤቶቿ ጋር በማያቋርጥ ግጭት ውስጥ እንድትኖር አድርጓታል።

በአሁኑ ወቅት ኤርትራ በገዥው ሻዕቢያ በተለይም በአዛውንቱ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ፍፁም አምባገነናዊ መዳፍ ሥር ትገኛለች። ሀገሪቱ ከተመሰረተች ጀምሮ ከኢሳያስ ውጭ ሌላ መሪ እይታም አታውቅም፡፡ ሰውየው በተደጋጋሚ በውጭ ጋዜጠኞች “ኤርትራ መቼ ምርጫ ታደርጋለች?” ተብሎ ሲጠየቅ ስላቃዊ ምላሹ “ምርጫ ምንድነው?” የሚል ነው፡፡

የቻታም ሃውስ የአፍሪካ ፕሮግራም የጂኦፖሊቲክስ ተንታኞች እንደሚያስጠነቅቁት፣ “በኤርትራ ውስጥ ተቋማዊ የሥልጣን ሽግግር ማዕቀፍ አለመኖሩ፣ የወደፊቷን ኤርትራ ከፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ሕልፈት በኋላ ለከፍተኛ የፖለቲካ አለመረጋጋትና ተቋማዊ መፍረስ ያጋልጣታል” ብለዋል፡፡ ድህረ-ኢሳያስ ኤርትራ ምናልባትም የተደራጀ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይል ባለመኖሩ እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የመግባት ዕድሏ ከፍተኛ ነው።

በአጠቃላይ፣ “የአፍሪካዋ ሲንጋፖር” ትሆናለች ተብላ የተጠበቀችው ኤርትራ፣ ዛሬ ላይ በዜጎቿ ስደት፣ በኢኮኖሚ ቁልቁለት ጉዞና በፖለቲካዊ ጭቆና ውስጥ የምትገኝ ሀገር ሆና አንድ ትውልድ ዕድሜ አስቆጥራለች። በነጻነትና ዴሞክራሲ የተንበሸበሸች፣ በኢኮኖሚ የተመነደገች ሀገር እንፈጥራለን ያሉት ኢሳያስ ኤርትራን ሳትነሳ የወደቀች ሀገር አድርገዋታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.