ስደት በስተርጅና ፡ የታሪክ መራራ መስታወት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በዕድሜ መገባደጃ ላይ ዕድሜ ልክ የለፉበትን ሀብትና ንብረት ጥሎ ለስደትና ለውርደት መዳረግ ከማንኛውም የፖለቲካ ሽንፈት በላይ የከፋ ሰብዓዊ ውድቀት ነው።ህገወጡ ህወሃትም የሆነው ይህንኑ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቆይታም የገለጹት ይህንኑ የሕዝብን መራራ ዕጣ ፈንታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይና እያንዳንዱ አስተዋይ ዜጋ ሊገነዘበው የሚገባ ወቅታዊ የደወል ጥሪ ነው።
እውነትም አስተውሎ ለሚመለከት ሕዝብ ላለፉት አምስት አሥርት ዓመታት ሕዝብን ለጦርነትና ለጥፋት ሲዳርጉ የነበሩ መሪዎች፣ ራሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ከአንዲት ጥይት ጭስ እንኳ ተጠብቀው በሰላም እየኖሩ ማየት ከእውነታ የራቀ ትልቅ የታሪክ ምጸት መሆኑ አያከራክርም።
ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ቆይታቸው ላልተመለሰው ወጣት “እነሱ በሀብትና በቅንጦት እየተንደላቀቁ አንተ ለምን ትሞታለህ? ለምንስ ትቆስላለህ?” ሲሉ ጠይቀው እያንዳንዱ ታጣቂ ወጣት ዛሬውኑ ሊጠይቀው የሚገባውን መሠረታዊ ጥያቄ ያነሱት።
ከዚህ አውድ አንጻር የኤርትራን ወቅታዊ መራራ እውነታ ማየት ትልቅ ትምህርት ይሰጣል። ትናንት በኢንዱስትሪና በንግድ እንቅስቃሴዋ ደማቅ የነበረችው ኤርትራ ዛሬ በስልጣን ጥመኞች የተሳሳተ ፖለቲካዊ ቁማር ሰለባ በመሆኗ ዕድገቷ ከስር መሰረቱ ተመናምኗል።
ሕዝቧም የልማትና የሰላም ባለቤት ከመሆን ይልቅ በየበረሃውና በባህር ዳርቻዎች ለስደትና ለእንግልት ተዳርጓል። ይህ የሚያሳየው ሀገርንና ወገናቸውን ለጠላት መጫወቻነት አሳልፎ መስጠት የሚያስከትለውን አስከፊ ታሪካዊ ውድቀት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንደገለጹት ፥ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረችበት ወቅት ከ300 በላይ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ያሏትና ከተሞቿ ያበቡ የነበሩ ቢሆንም፣ የአገዛዙ እኩይ መንገድ ግን ከተሞቿን አድብቶ አስመራን ከአርባ ምንጭና ከጅግጅጋ የምታንስ የመንደር ያህል አድርጓታል፤ ምጽዋና አሰብም ባዶአቸውን ቀርተዋል፤ የኤርትራ አገዛዝ ልማትንና ተቋማትን መገንባት ትቶ የኢትዮጵያ ጠላቶች መጫወቻ በመሆኑ፣ ሥራ ወዳዱና እንግዳ ተቀባዩ ሕዝቧ ዛሬ ለስደትና እንግልት ተዳርጓል።
በትግራይም የተከሰተው ይኸው አደጋ ነው፤ የሕገወጡ ሕወሓት እኩይ ፍላጎት እና ማለቂያ የሌለው የስልጣን ጥማት የትግራይን ሕዝብ ሕይወት ወደ ማያባራ የጦርነት አውድማ በመክተት ከባዱን የመከራ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል።
ለግል ጥቅማቸውና ለእብሪታቸው ያደሩ የፖለቲካ ነጋዴዎች አላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ሚሊዮኖችን ወደ እሳት ይማግዳሉ፤ እናቶች ልጆቻቸውን በከንቱ ያጣሉ፣ ነዋሪዎች ይፈናቀላሉ፣ መሰረተ ልማቶችም ወደ አመድነት ይቀየራሉ።
ይህ ጥፋት በአጋጣሚ የተፈጠረ ሳይሆን ለረጅም ዘመናት በስሌት የተቀነባበረ የፖለቲካ ሴራ ነው። በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት በሕወሐት ዕንቅፋትነት ሳይሳካ የቀረ ሲሆን፣ ሰላምን ያልፈለገው አመራር ለአራተኛ ጊዜ የጀመረው አውዳሚ ጦርነትም ለአራተኛ ጊዜ በሽንፈት ተጠናቋል።
ወጣቶችም ጊዜው ሳይረፍድባቸው ወደ ኋላ-ቀርነትና ውድመት የሚመራውን የጥፋት መንገድ በመተው ፣ ትጥቃቸውን በመፍታት ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ሊመለሱ ይገባል።
የጦርነት ጠማቂ የሆኑት የህገወጡ ቡድን መሪዎችም ቢሆኑ በስተርጅና ዕድሜያቸው ተንከራታች ስደተኛ ከመሆንና ሃገርን ከማፍረስ ተቆጥበው በሰላም እጃቸውን መስጠት አለባቸው።
ዛሬ የሕገ-ወጡ ሕወሓት ቡድን የጥፋትና የቁማር ፖለቲካ አሁን በይፋ አብቅቷል። የትግራይ ሕዝብ ከግጭት አዙሪት ወጥቶ የራቀውን ሰላም እንዲጎናጸፍ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱ እንዲረጋገጥና የልማት ትሩፋቶችን ማጣጣም እንዲችል በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር ተመሥርቷል።
ሕዝቡም ከጦርነት መከራ ወጥቶ ወደ ልማትና ብልጽግና የሚያደርገው ጉዞ አሁን በጽኑ መሠረት ላይ ቆሟል።
ለሚቀጥሉት 6 ወራት ክልሉን የሚያስተዳድረው ይህ ባለአደራ አስተዳደር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች፣ የግዛት አንድነትና የትግራይን ሕዝብ መሠረታዊ ጥቅሞች መሠረት በማድረግ የሚሰራ ይሆናል።