የሀገር መከላከያ ሠራዊት – የ119 ዓመታት የጀግንነት፣ የሉዓላዊነትና የዘመናዊነት ጉዞ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የ119ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ሲያከብር፣ በረጅም ዘመናት ታሪኩ ደምቀው የተመዘገቡ የጀግንነት፣ የጽናትና የሀገር ፍቅር ስኬቶችን በመዘከር ነው።
ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ባስቆረው የተቋሙ እድሜ በተካሄዱ የሀገርን ዳር ድንበር የማስከበር ተልዕኮዎች፣ ሠራዊቱ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና ነጻነት በደሙና በአጥንቱ አስከብሮ የታፈረችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለዚህ ትውልድ አድርሷል።
የሀገርን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስከበር፣ የሕዝብን ደኅንነት ማረጋገጥና ሕገ-መንግሥቱንና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማስከበር የሠራዊቱ የዘመናት ታሪካዊ አደራዎች ናቸው፤ በአሁኑ ወቅትም እነዚህን ግዴታዎች በብቃት መወጣት የሚያስችል አዲሱን የዘመናዊነትና የብቃት ደረጃ ተጎናጽፏል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ በሀገር ውስጥ ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን በጀግንነት ከመፈፀም ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ በተከናወኑ የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የተጣለበትን ኃላፊነት በከፍተኛ የሙያ ሥነ-ምግባርና በጀግንነት በመወጣት የሀገራችንን ስም በዓለም አቀፍ መድረክ አስጠርቷል።
በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችና አለመረጋጋቶች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የየተሳሰሩ በመሆናቸው፣ የሽብርተኝነትንና የጽንፈኝነት አደጋዎችን ለመግታት የሀገር መከላከያ ሠራዊት የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር በተካሄደው ተቋማዊ የሪፎርም፣ መከላከያ ሠራዊቱን ወደ አዲስ የዘመናዊነትና የተቋማዊ ብቃት ምዕራፍ እንዲሸጋገር አስችሎታል፡፡
በተተገበረው ተቋማዊ ሪፎርም መሰረት ሠራዊቱ በዘመናዊ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች፣ በሰው አልባ የውጊያ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) እና በላቁ የጦር መሣሪያዎች እንዲታጠቅ ተደርጓል።
በአሁኑ ወቅት ሠራዊቱ በምድር ኃይል፣ በሜካናይዝድ፣ በአየር ኃይል፣ በዘመናዊ መልኩ እንደገና በተደራጀው የባህር ኃይል፣ በልዩ ኦፕሬሽን ኃይሎች እንዲሁም በሳይበር ደህንነት ዘርፎች በተሟላ መልኩ ተዋቅሮ ዘመኑን የዋጀ የሀገር ጋሻ መከታ በሚደርገው ቁመና ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ የሀገሪቱን ሉዓላዊ ግዛትና ብሔራዊ ጥቅሞች ከአየር፣ ከምድር፣ ከባህርና ከሳይበር ጥቃቶች የመጠበቅ ሙሉ ዝግጁነት አለው። ሠራዊቱ የሀገር አለኝታ፣ የሕዝብ ከለላ እና የቀጠናዊ መረጋጋት ዋስትና መሆኑን በተግባር አስመስክሯል።
ኢትዮጵያ የሚገጥሟትን ፈተናዎች በድል ለመሻገር የሚያስችል፣ ሰላሟን የሚያጸና፣ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚስጠብቅ እና የብልፅግና ጉዞዋን የሚፋጥን ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ ሠራዊት ገንብታለች፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ