በትግራይ ክልል የንግድ እንቅስቃሴን የማነቃቃት እና ገበያን የማረጋጋት ስራዎች እየተከናወኑ ነው -ባለአደራ አስተዳደሩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል የንግድ እንቅስቃሴን የማነቃቃት እና ገበያን የማረጋጋት ስራዎች እየተከናወኑ ነው አሉ በክልሉ የባለአደራ አስተዳደር የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር)።
ዋና አስፈጻሚ ቴዎድሮስ እንደገለጹት፤በክልሉ የባለአደራ አስተዳደር ከተቋቋመ ጀምሮ የተጎዱ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ መዋቅሮችን በመዘርጋት እና ችግሮች በማቃለል ህዝቡ ወደ መደበኛ ህይወቱ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
በትግራይ ክልል በሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ምክንያት ተቋርጠው የቆዩ መደበኛ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የመሰረተ ልማቶች አውታሮች ወደ መደበኛ ስራቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡
በሕገ ወጡ ሕወሓት የፈረሱ የመንግስት መዋቅሮች መልሶ ለመዘርጋት እና የሕዝብ አገልግሎቶች ለማስቀጠል ጊዜያዊ አስተባባሪዎችን በመመደብ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ገበያ እንዲነቃቃ እና የምግብና የምግብ ነክ ሸቀጦች እንዲሟሉ ባለአደራ አስተዳደሩ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም የአቅርቦት እጥረቱ እየተቀረፈ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የህዝብ የንቅናቄና የውይይት መድረኮች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የተናገሩት ስራ አስፈጻሚው÷ ከየመድረኩ የሚነሱ የህብረተሰቡ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ ለችግሮች ምላሽ እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
የፍጆታ አቅርቦትን ለማሟላትና የንግድ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እና ገበያን ለማረጋጋት ከባለሃብቶች፣ ባንኮች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የምግብ እና የምግብ ነክ ዓይነቶች ወደ ክልሉ እየገቡ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡
በመቐለ ከተማ አስተዳደር የተጀመረውን የመማር ማስተማር ሂደት በሁሉም አካባቢዎች ለማስጀመር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡