Fana: At a Speed of Life!

የጣና ፎረም ኢትዮጵያ የቀጣናው ሰላምና ደህንነት መልህቅ መሆኗን የሚያሳይ ነው – የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የጣና ፎረም ኢትዮጵያ የቀጣናው ሰላምና ደህንነት መልህቅ መሆኗን የሚያሳይ ነው አሉ የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ።
“በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦ ፖለቲካ ለውጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 13 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ በባሕር ዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው 12ኛው የጣና ፎረም በስኬት ተጠናቋል።
ይህንን አስመልክተው የኢትዮጵያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት÷ የጣና ፎረም የአፍሪካ መሪዎች በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ግልጽ ውይይት የሚያደርጉበት ስኬታማ መድረክ ነው።
መድረኩ ሰዎች ንግግራቸውን በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ሳያሽሞነሙኑ ሀሳባቸውን እንደ ልባቸው የሚገልጹበት መሆኑን እና ይህም ከሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ጣና ፎረም ባለፉት 12 ዓመታት ተገቢ ምክረ ሀሳቦችን በማቅረብ ለአፍሪካ ሕብረት የአህጉሪቷን ሰላምና ደህንነት ሪፖርት በማዘጋጀት ገንቢ ሚና መወጣቱን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የቀጣናው መልህቅ ናት፤ በቀጣይም ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ያላትን ቁርጠኝነት አጠናክራ መቀጠል አለባት ያሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመፍትሔ አማራጭ በማቅረብ እና ሰላምና ደህንነት የምታበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ለሰላምና ጸጥታ በምታደርገው ጥረት የቀጣናው መልህቅ ሆና መቀጠሏን በተግባር የሚያረጋግጥና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም አመልክተዋል።
ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ የውስጥ፣ የቀጣና፣ የአህጉሪቷና የዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ትኩረት የምትሰጠው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አንስተው የኢትዮጵያ መንግሥት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ በሚሰጠው ቁርጠኝነት መሰረት የሚያቀርበው ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪም ይህንን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
መንግሥት ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ፣ በውይይት፣ በድርድርና በሰጥቶ መቀበል መርህ ለመፍታት ብዙ ርቀት መጓዙን ገልጸው ለዚህም ከአዋጅ ባሻገር ወደ ተግባራዊ እርምጃ ተሸጋግሯል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.