በ4 ዓመታት ውስጥ የሀገር ውስጥ መድኃኒት አቅርቦትን ከ8 ወደ 44 በመቶ ማሳደግ ተችሏል – (ዶ/ር) መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት 4 ዓመታት ባከናወነቻቸው የጤና ዘርፍ ሪፎርሞች የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦትን ከ8 በመቶ ወደ 44 በመቶ ማሳደግ ተችሏል አሉ የጤና ሚኒስትር (ዶ/ር) መቅደስ ዳባ።
19ኛው ዓለም አቀፍ የሕክምና ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
(ዶ/ር) መቅደስ ዳባ በመድረኩ ላይ፤ በጤና ዘርፍ ከተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎች መካከል የጤና ተቋማትን መሠረተ ልማትና ተደራሽነት ማሻሻል፣ የሕክምና መሣሪያዎችንና የመድኃኒት አቅርቦትን ማሳደግ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን አቅም መገንባት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦትን ከ8 በመቶ ወደ 44 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ገልጸው ይህም አፍሪካ በፈረንጆቹ 2040 ሥልሳ በመቶ የሚሆነውን የመድኃኒት ፍላጎቷን በራሷ አቅም ለመሸፈን ለያዘችው ዕቅድ ጉልህ መሠረት እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና የዘርፉን አፈጻጸም ለማሻሻል ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ አሠራሮችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
ከጤናው ዘርፍ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን ተቋማት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሠራር ሥርዓት በማስተሳሰር ቅንጅታዊ አሠራርን ለማጠናከርም እየተሠራ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።
ጉባኤው በጤና ዘርፉ የተቀናጀ አሠራርን ለማጠናከር፣ የተለያዩ አካላትን ትብብር ለማሳደግና ልምድ ለመለዋወጥ ጉልህ ሚና አለው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።