ለአፍሪካ ከእስካሁኑ የተለየ፣ ተሻጋሪ፣ ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት ያስፈልጋታል-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “ለአፍሪካ ከእስካሁኑ የተለየ፣ ተሻጋሪ፣ ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት ያስፈልጋታል” ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
7ኛው የአፍሪካ የስታቲስቲክስ ቀን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አማካኝነት ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት በቨርቹዋል ውይይት መከበር ተጀምሯል።
ውይይቱም “የአሥርት ዓመታቱን የአፍሪካ ብሔራዊ የስታቲስቲካል ሥርዓት ከዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ተጽዕኖ ለማውጣት የሚያስችል ቀጠናዊ መፍትሄ ማበጀት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ውይይቱን በይፋ ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት አህጉሪቱ የመረጃ ሥርዓቷን የምታዘመንበት አሰራር መዘርጋት ይጠበቅባታል።
አህጉሪቱ የያዘቻቸውን ዘላቂ የልማት አጀንዳና የአፍሪካ ህብረትን ብሔራዊ የልማት ዕቅድ ለማሳካት ጥራት ያለው መረጃ ያስፈልጋታል ብለዋል።
የአፍሪካ የመረጃ ሥርዓት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት “ከፍተኛ” ተዕእኖ እንዳሳደረበት ያመለከቱት ፕሬዚዳንቷ፥ ወረርሽኙ ካሳደረበት ችግር ለማውጣት ሀገራት በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
በአህጉሪቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመርጃ ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግም መረጃን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ በመቅረጽ ምርትን ለማሳደግ፣ የህዝብን ፍላጎት ለማሟላትና ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ይረዳል ብለዋል።
የአፍሪካውያንን ጾታዊ እኩልነት ለማረጋገጥም ዘመኑ የሚጠይቀውን ሥርዓት መዘርጋት ወሳኝ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።