ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረጉ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ሰብአዊ ድጋፍ እያደረጉ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቀረቡ።
አቶ ደመቀ መንግስት በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል በሰብዓዊ ድጋፍ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አጋር አካላት በሰብአዊና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ሁለተኛ ዙር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም በሰብዓዊ ድጋፍ ወቅት እየተከሰቱ ላሉ ተግዳሮቶች ዋነኛው ተጠያቂ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሆኖ ሳለ፥ ዓለም አቀፍ ተቋማቱ ግን መንግስትን ተጠያቂ ማድረግ መርጠዋል ነው ያሉት።
መንግስት ለዜጎች ሰላምና ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት የተናጥል ተኩስ አቁም ቢደርስም፥ አሸባሪው ህወሓት የተኩስ አቁሙ መጣሱን አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈም በአማራና አፋር ክልሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጥቃቶችን እየፈጸመ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች የፌደራል መንግስቱን የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና ሰብአዊ መብት ድጋፎችን አጠናክሮ ለመቀጠል ላሳየው ቁርጠኝነት እውቅና መስጠታቸውን አመስግነዋል፡፡
ድጋፉ በተሻለ መልኩ እንዲቀጥል አሸባሪውን ቡድን በማውገዝና እኩይ ተግባራቱ እንዲያቆም ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
አሁን ላይ በሁለቱ ክለሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እየደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ደመቀ÷ እስካሁን ባለው ሂደት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሶስት ዙር አፋር ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
መንግስት በትግራይ ክልል ካለው ሰብዓዊ ድጋፍ ጋር በተያያዘ የሃገሪቱን የደህንነት ሁኔታ በማይጎዳ መልኩ ሰብዓዊ ድጋፉ ለዜጎች እንዲደርስ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
ይሁን እንጂ መንግስት የሃገሪቱን ሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነት የሚጻረሩ ማናቸውንም ሁኔታዎች አይታገስም ነው ያሉት።
ድርጅቶቹ በቀጣይ የሚያደርጉት ሰብዓዊ ድጋፍ በአማራ እና አፋር ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆንም ነው የጠየቁት።
በወንደሰን አረጋኸኝ