Fana: At a Speed of Life!

በደብረብርሃን ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ

 

አዲስ አበባ፣ህዳር 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ፈጥኖ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሊያደርግልን ይገባል ሲሉ ከተለያዩ ዞኖች ተፈናቅለው በደብረብርሃን ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ጠይቀዋል።

ተፈናቃዮቹ አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ባደረሰባቸው ግፍ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በደሴ መጠለያ መቆየታቸውን ገልፀው አሁንም ለዳግም ስደት ተዳርገናል ብለዋል ።

እስካሁን የደብረብርሃን ከተማ ነዋሪዋችና በጎ አድራጊዎች እያገዟቸው መሆኑን ያነሱት ተጎጅዎቹ÷ በመጠለያ ጣቢያዎቹ ህፃናት፣ ነፍሰጡሮችና አቅመ ደካሞችን ታሳቢ ያደረገ ድጋፍ መንግስት ፈጥኖ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን እስካሁን ከ219 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አበባው መለሰ ተናግረዋል።

አሁን ላይ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎችን በማዘጋጀት ዞኑና ክልሉ ያለውን የመጠባበቂያ ሀብት በመጠቀም እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጅ እስካሁን ከመንግስት ለተፈናቃዮች የመጣ ድጋፍ አለመኖሩን አስረድተዋል።

የተፈናቃዮች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ ቢሆንም ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶችን ጨምሮ መሰል ተቋማት እገዛ እያደረጉ አለመሆኑንም ነው የገለጹት።

አያይዘውም ለተጎጅዎች ፈጥኖ ለመድረስ እገዛ ስለሚያስፈልግ መንግስት፣ የረድኤት ድርጅቶች እና መላው ህዝብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በአበበ የሸዋልዑል

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.