በከተማዋ ህገ ወጥ የመስመር ዝርጋታና የኃይል ስርቆት ተፈጽሟል-የኤሌክትሪክ አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ህዳር 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ስሙ ሰፈራ (ቦርሱማ)በተባለ አካባቢ በህገወጥ መንገድ የመስመር ዝርጋታና የኃይል ስርቆት መፈፀሙን የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
ወንጀሉ የተፈፀመው በአካባቢዉ በሚኖሩ አንዳንድ ግለሰቦችና ከሌሎች ህገወጥ አካላት ጋር በመተባበር መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት ጥቆማ እንደሆነ አገልግሎቱ ገልጿል፡፡
ስርቆቱ የተፈፀመው ከልማት ተነሺዎች ላይ ቆጣሪ፣ የኤሌክትሪክ ምሰሶና ገመድ በመውሰድ መሆኑን ገልፆ፥ ነዋሪዎቹ ያላግባብ የኤሌክትሪክ ኃይል ለግል ፍጆታና ለንግድ ተግባር ሲያውሉ ተደርሶበታል ብሏል፡፡
የህገ ወጥ የመስመር ዝርጋታና የኃይል ስርቆት በተለያዩ ጊዜያት የሚፈፀም ሲሆን ፥ የሃገርን ሃብት ለግል ጥቅም ለማዋል ሲባል በህጋዊ መንገድ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ ማነቆ እየሆነ መሆኑን የመዲናዋ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቋል፡፡
በአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ በዲስትሪክትና በአገልገሎት መስጫ ማዕከል እንዲሁም ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የተሰረቀውን ንብረት በትላንትናው ዕለት ማስመለስ መቻሉንም ተገልጿል፡፡
እንደነዚህ አይነትና መሰል ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ብሎም ከስር መሰረቱ ለማጥፋት ሁሉም ህብረተሰብና የፀጥታ አካላት በባለቤትነት ስሜት ሊጠብቅ እንደሚገባም ከአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።