የህዝቡ እንቅስቃሴ ወኔ የሚያሰንቅ እና የጠላትን አንገት የሚያስደፋ ነው- የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ
አዲስ አበባ፣ ኅዳር 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪዎቹን ህወሓት እና ሸኔን ለመመከት ህዝቡ ለህልውና ዘመቻው የሚያደርገው እንቅስቃሴ ወኔ የሚያሰንቅ እና የጠላትን አንገት የሚያስደፋ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ ገለጹ፡፡
ወያኔ እና ሸኔ የቆዬ ትስስር ነው ያላቸው የሚሉት ሃላፊው÷ የኦሮሞ ህዝብ ትግል እንቅስቃሴ ፍሬ እንዳያፈራ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ታዋቂ ግለሰቦች እና አርሶ አደሮችን ጭምር ሲያስገድሉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ህወሓት ግጭቶች ሁሉ የብሄር መልክ እንዲይዙ ማድረግ፣ አልፎ አልፎም የሃይማኖት መልክ እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረቶችን ሲያደርግ ነበር ነው ያሉት፡፡
የሰላም ጉዳይ ሲነሳ የጸጥታ አካላት ስራ ብቻ አይደለም፤ ሰላም ሲናጋ ተጎጂው ህብረተሰቡ ስለሆነ ህዝቡ ሃላፊነቱን እንዲወጣ የተለያዩ አደረጃጀቶችን ፈጥረን አካባቢን ለመጠበቅ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ሃላፊው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ ለጥፋት ተልዕኮ ሊሰማሩ የነበሩ በሺህ የሚቆጠሩ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አንስተዋል፡፡
እነዚህን ጸረ-ኢትዮጵያ የሆኑ ሃይሎችን ለመቋቋም የኦሮሞ ህዝብ ልጆችን ህጋዊ በሆነ መንገድ በልዩ ሃይልና በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ እየተሳተፉ እና እየታገሉ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የኦሮሞ ወጣቶች ጣና ላይ ተገኝተው እንቦጭን ለመንቀል ያደረጉት ተግባር ስለ ሀገር ያገባኛል አስተሳሰብና ስሜት በተለይም በአማራና ኦሮሞ ህዝቦች መካከል ያለውን መናበብ ያረጋገጠ ነበር ሲሉም ያስታውሳሉ፡፡
ኢትዮጵያ በውጭ ጫና ስር መሆኗን ያነሱት አቶ ሁይሉ÷ ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን ግብርናውን ለማዘመን በክልሉ በበጋ ስንዴ ምርት፣ በመስኖና እርሻ ስራ እንዲሁም በምርት አሰባሰብ ሂደት ላይ የተከናወኑ ተግባራትን ጠቅሰው ይሄም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በሻምበል ምህረት
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!