የኢትዮጵያ ጠንካራ አጋር መሆን የምትፈልገው ሮማኒያ …
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሮማኒያ ፕሬዚዳንት ከፍተኛ አማካሪ ዳቺያን ቺዮሎሽ ሮማኒያ በተለያዩ ዘርፎች የኢትዮጵያ ጠንካራ አጋር መሆን ትፈልጋለች አሉ፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የሮማኒያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአሁኑ የሀገሪቷ ፕሬዝዳንት ከፍተኛ አማካሪ ዳቺያን ቺዮሎሽን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚህ ወቅት ከፍተኛ አማካሪው ኢትዮጵያ ለውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ክፍት ያደረገቻቸው አዳዲስ አሰራሮች ለሮማኒያ ባለሀብቶች ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናም ሆነ በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ ለሮማኒያ እጅግ ወሳኝ አጋር መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡
ዘንድሮ ሮማኒያ በአዲስ አበባ ኤምባሲ የከፈተችበትን 60ኛ ዓመት እንደምታከብር አስታውሰው፤ ይህ አጋጣሚ የቆየውን ወዳጅነት ዳግም ለማነቃቃትና የወደፊት ትብብርን ለማጠናከር ትልቅ መሰረት እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ባለፉት አሥርት ዓመታት በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን በሮማኒያ ከፍተኛ ትምህርታቸውን የመከታተል ዕድል ማግኘታቸውን ገልፀው፤ ይህንን ባህል በማስቀጠል አዳዲስ የትምህርት ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም በኢኮኖሚ ትብብር መስክ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ እና የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
በፖለቲካዊ መስኮች እና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ በጋራ መስራት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች እና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ግንኙነቱን ማስፋፋት የጉብኝቱ ዋነኛ ዓላማዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
አማካሪው አዲስ አበባን የጎበኟት ከ12 ዓመታት በፊት እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የታየው ፈጣን ለውጥ እና ዕድገት እንዳስገረማቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሮማኒያ በኢኮኖሚው ዘርፍም ሆነ በሌሎች የልማት መስኮች የኢትዮጵያ እውነተኛ እና ጠንካራ አጋር ሆና ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላት ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡