Fana: At a Speed of Life!

ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነታችን ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ወሳኝ ሀይል እንድትሆን አድርጓታል – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነታችን ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ወሳኝ ሀይል እንድትሆን አድርጓታል አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።

የአገልግሎቱ መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተቋማዊ ጥንካሬንና የዜጎችን ክብር ያረጋገጠ አዲስ የዲፕሎማሲ አድማስ!!

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መሠረታዊ ዓላማ የዜጎቻችንን ሁለንተናዊ ክብር ማስጠበቅና የጋራ ብሔራዊ ጥቅማችንን ማረጋገጥ ነው። ይህ ፖሊሲያችን “ቅድሚያ ለጎረቤት” የሚል ጥልቅ ወንድማማችነትን ያነገበ ሲሆን፣ በቀጠናዊ ትስስርና በፓን አፍሪካኒዝም እሴቶች መረትነት የተገነባ ነው። “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” የሚለው መርሐችን አገራችን ከአህጉራዊ ወንድሞቿ ጋር በመተባበርና በመደጋገፍ የጋራ ብልጽግናን ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ይህም ዲፕሎማሲያችን ከመንግሥታዊ ግንኙነት ባለፈ፣ በሕዝቦች መካከል ያለውን ትስስር የሚያጠናክርና ለሰው ልጅ ክብር ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን ያረጋግጣል።

የአገራችንን ሰላምና የሕዝባችንን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ፣ ኢትዮጵያ ማንኛውንም ዓይነት ትንኮሳ አስቀድሞ የመግታት አቅሟን በተጨባጭ ግዝፈትና ዝግጁነት ከፍ አድርጋለች። ይህ የመከላከል አቅም ዜጎቻችን ሉዓላዊ ሀገር እንዲኖራቸውና ልጆቻችን የነገ ተስፋቸው እንዲያብብ ዋስትና የሚሰጥ የማይታለፍ አጥር ነው። ለዚህም የመከላከያ ሠራዊታችንን በየብስ፣ በአየር ኃይል፣ በባሕር ኃይልና በሳይበር ደኅንነት ዘርፎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በተደራጀ ተቋማዊ ግንባታ አዘምነናል። ይህ ተጨባጭ የጥንካሬ መሠረት አገርን ከጥቃት የመከላከል ብቃት ብቻ ሳይሆን፣ የቀጠናው የሰላም ዓምድ ሆኖ የማገልገል ትልቅ ኃላፊነትም ጭምር ነው።

መንግሥት በዓለም አቀፍ መድረክ ያለውን አሳማኝ ተጽዕኖ የማሳደር አቅም ከአገራዊ ተጨባጭ ጥንካሬዎች ጋር በማቀናጀት ስትራቴጂያዊ የበላይነትን እየፈጠረ ይገኛል ። በሐሳብ የበላይነትና በአሸናፊነት መንፈስ ላይ የተገነባው ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነታችን ከመረጃ አቅም ብቃት ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ወሳኝ ሀይል እንድትሆን አድርጓታል።

ይህ የተቀናጀ አካሄድ አገራችን በዓለም አቀፍ ድርድሮችና ግንኙነቶች ወቅት የራሷን ፍላጎት በብቃት እንድታስከብርና በጎ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን እንድታጎላ አስቻይ ዓውድ ፈጥሮላታል። በዲፕሎማሲው ረገድ የተከተልነው ስልታዊ የአቀራረብ ለውጥ ከመከላከያ አቅማችን ጋር ተሳስሮ አገራዊ ጥቅማችንን በጽኑ መሠረት ላይ እንዲጸና አድርጎታል።

የኢትዮጵያ የመግታት አቅምና የዲፕሎማሲ ስኬት ምንጮች ወታደራዊ ዝግጁነት ብቻ ሳይሆኑ፤ የጠነከረ ኢኮኖሚ፣ ጽኑ አገራዊ መረጋጋትና የማይበገር ሕዝባዊ አንድነት ናቸው። እነዚህ የጥንካሬ መሠረቶች ተዳምረው አገራችንን በቀጠናውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷ ከፍ ያለ፣ ክብሯ የተጠበቀና ጠንካራ መንግሥት ያላት አገር እንድትሆን አድርገዋታል። መንግሥት ይህን የተገነባ አቅም ይበልጥ በማጠናከር፣ ዜጋ ተኮር የሆነውን የውጭ ግንኙነትና የአገርን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.