የተለያዩ ተቋማት እንዲሁም አመራሮችና ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አስረከቡ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን እንዲሁም የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አመራሮችና ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ለአገር መከላከያ ሰራዊት እና በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች 23 ሚሊየን ብር የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በዓይነት የተደረገው ድጋፍ የስንቅ፣ የንፅህና መጠበቂያ፣ አልባሳት እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶን ያካተተ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በድጋፍ ርክክቡ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት÷ ዜጎች ለአንድ አላማ ፀንተው ከቆሙ የተሻለ ውጤት የማይገኝበት መንገድ አይኖርም።
ሀብቱ የተሰበሰበው በቢሮው ስር ከሚገኙ ኮሌጆች አሰልጣኞች፣ ሰልጣኞች፣ የአስተዳደር ሰራተኞች እና የአይሲቲ ተቋማት መሆኑን የአዲስ አበባ ቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን ሃብቱ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ለጀግናው ሀገር መከላከያ ሠራዊትና በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ግምታቸዉ 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሆኑ የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የንጽሕና መጠበቂያና አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለሰሜን ሸዋ ዞን ድጋፍ አድርጓል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ÷ አገር ውስጥ የሚገኙ የምግብና የመድኃኒት አምራቾችን፣ አስመጪዎችና አከፋፋዮችን በማስተባበር ነው ድጋፉ የተደረገው ብለዋል፡፡
ባለስልጣኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትንና የተቋሙን ሰራተኞች በማስተባበር ለሀገር ህልዉና እየተፋለሙ ላሉና በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች እስካሁን 10 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ሲሳይ ወ/አማኑኤል በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ያደረገው ድጋፍ ለጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖቻችን የሚውሉና የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የላቀ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና ሰራተኞች በቢሾፍቱ መከላከያ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመገኘት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት የተለያየ የአይነት ድጋፍ አስረከቡ፡፡
ድጋፉ በዋናነት በክፍለ ከተማው ጤና ጽ/ቤት አስተባባሪነት የተሰበሰበ ሲሆን÷ የህክምና መስጫ መሳሪያዎች፣ ሰንጋዎች፣ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች፣ ፍራሽ እና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡
ክፍለ ከተማው ከዚህ ቀደም በተለያዩ ግምባሮች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የፀጥታ ሃይሎች የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል መባሉን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡