ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ላይ የሚደረግባትን ማንኛውንም ጫና እንደማትቀበል አምባሳደር ዘነበ ከበደ ገለጹ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 8 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ላይ የሚደረግባትን ጫና እንደማትቀበል በጄኔቭ የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዘነበ ከበደ ገለጹ።
አምባሳደር ዘነበ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ በጠራው ልዩ ስብሰባ ላይ በበይነ መረብ ተሳትፈዋል።
አምባሳደሩ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ላይ ጫና ለማድረግ ለሚቃጣ ለማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴና አሰራር እንደማትተባበር እና ይህን መሰል ጫና እንደማትቀበል ገልጸዋል።
የተመድ የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት በአንዳንድ ምዕራባውያን አገሮች የፖለቲካ ጫና ለማሳደር የሚያገለግል መሳሪያ ሆኗልም ነው ያሉት አምባሳደሩ።
የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ሃላፊነት እና ስልጣንም በገለልተኝነት ማገለግል እንጂ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳን ማስፈጸም እንዳልሆነ በአጽንኦት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጠ መንግስት፣ የውስጧን ሰላም እና የህዝቦቿን የወደፊት እጣ ፋንታ ለማስጠበቅ በምታደርገው ጥረት በምክር ቤቱ ኢላማ ተደርጋ መገለል ደርሶባታል ሲሉም አስረድተዋል።
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተነሳው ግጭት ሳቢያ ተፈጽሟል ከተባለው ሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘም፥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዋና ፅህፈት ቤት በጋራ ምርመራ ማድረጋቸውን አምባሳደር ዘነበ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ለሰብአዊ መብት ትልቅ ግምት የሚሰጥ መንግስት እንዳላት በማንሳትም፥ መንግስት በሁለቱ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት የቀረበውን ምክረ ሃሳብ ለመተግበርና ለዚህ እንዲረዳም ብሄራዊ ኮሚቴ እና የሚኒስትሮች ግብረ ሃይል ማቋቋሙ ቁርጠኝነቱን ያሳያል ብለዋል።
ምክር ቤቱ የጠራው ልዩ ስብሰባ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ከመሞከር ባለፈ በአሸባሪው ህወሓት የተፈጸመውን አስገድዶ የመድፈር፣ የንብረት ውድመት እና ህጻናትን ለጦርነት መጠቀም የመሳሰሉ ወንጀሎችን አለማውገዙን በማንሳት አካሄዱን በጥብቅ ነቅፈውቷል።
ከዚህ ባለፈም አሸባሪ ቡድኑ ለትግራይ ክልል ነዋሪዎች ሰብአዊ እርዳታ ማጓጓዣነት የሚውሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎችን በመያዝ ለፖለቲካዊ እና ለጦርነት ተግባር ጥቅም ላይ ማዋሉን አንስተዋል።
ቡድኑ የምግብ መጋዘኖችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጭምር አውድሟል ያሉት አምባሳደር ዘነበ፥ የልዩ ስብሰባው ተሳታፊዎች ግን ፍላጎታቸውን በመንግስት ላይ ለመጫን መወሰናቸውን አይነግሩንም፤ የዚህ ስብሰባ እኩይ ዓላማም ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳን ማስፈጸም ነው ብለዋል።
አያይዘውም ሃላፊነት በተሰጠው አካል በጉዳዩ ላይ ምርመራ ተደርጎና ተጠናቆ እያለ ያንኑ ተመሳሳይ ስራ የሚሰራ ሌላ አካል ለምን ማቋቋም አስፈለገ ? ሲሉም የልዩ ስብሰባውን አካሄድ ጠይቀዋል አምባሳደሩ። አካሄዱንም አሸባሪውን ቡድን ማበረታታትና ሁኔታውን ማባባስ ነው ብለውታል።
ኢትዮጵያ እንደተመድ መስራች አባልነቷ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ አድናቂና ተከታይ መሆኗን ያነሱት አምባሳደር ዘነበ፥ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ለባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ያደረገችው ጥረት ራሷን ለመከላከል እያገዛት አለመሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ እሳቤም አሁን ላይ የኒኮሎኒያሊስት አስተሳሰብ በሚያራምዱ ሃይሎች ተጠልፏል ነው ያሉት።