በውጫሌ ከተማ አራት የቤተሰብ አባላት በሽብር ቡድኑ በተተኮሰ መድፍ ተገድለዋል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጫሌ ከተማ አራት የቤተሰብ አባላት በአሸባሪው ህወሓት በተተኮሰ መድፍ መገደላቸውን የአይን እማኞች ተናገሩ።
‘ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እወርዳለሁ’ በማለት የጥፋት እጁን የዘረጋው አሸባሪው ህወሓት በንጹሃን ዜጎች ላይ ያልፈጸመው አይነት ሰቆቃ የለም ተብሏል።
የሽብር ቡድኑ የመከላከያ ሠራዊትና የጸጥታ ኃይሎችን ምት መቋቋም ሲሳነው ንጹሃንን መግደልና ሀብትና ንብረት ማውደምን መገለጫው አድርጎታል።
የውጫሌ ከተማ ነዋሪው ሃምሳ አለቃ ፈንታዬ ሞላ ከሽብር ቡድኑ ጥቃት ሰለባዎች አንደኛው ናቸው።
የሽብር ቡድኑ ወደ ውጫሌ ከተማ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ አራት የቤተሰባቸውን አባላት ሲገድል ሌሎች አራቱን ደግሞ ከባድ የመቁሰል አደጋ እንዳደረሰባቸው ይናገራሉ።
ሃምሳ አለቃ ፈንታዬ በሽብር ቡድኑ የከባድ መሣሪያ ድብደባ ባለቤታቸውን፣ የልጃቸውን ሚስት እንዲሁም የወንድማቸውን ልጆች አጥተዋል ነው የተባለው፡፡
ሁለት መኖሪያና አንድ ኩሽና ቤት ሙሉ በሙሉ ሲወድምባቸው ስድስት በጎቻቸውም መሞታቸውን ተናግረዋል።
በወቅቱ የአካባቢው ሰው በስጋት ምክንያት መውጣት ባለመቻሉ አራት አስክሬን ይዘው ማደራቸውንና ሲነጋም ራሳቸው እየዞሩ ቤተሰቦቼ አልቀዋል አቃብሩኝ ብለው ተጣርተው መቅበራቸውን ነው የገለጹት።
የሟች ቤተሰብ የሆኑት ወይዘሮ አረጋሽ ሀይሌ፥ ድብደባው በተፈጸመበት ቅጽበት ከቦታው ቢደርሱም ሶስቱ ሕይወታቸው አልፎ እንዳገኟቸው እና አራተኛዋም ክንዳቸው ላይ አቅፈዋት ሕይወቷ ማለፉን ገልጸዋል።
እናትና ባለቤቱን በአንድ ጊዜ የተነጠቀው የሃምሳ አለቃ ፈንታዬ ልጅ አቶ ገበየሁ ፈንታዬም “በወቅቱ አራት የቤተሰቦቻችንን አባላት አጥተን ‘ማልቀስ አትችሉም’ ተብለን ተከልክለናል” ነው ያለው።
ከአንድ ቤተሰብ አራቱ ሞተው፣ አራቱ ቆስለው፣ ስድስት በጎች ተገድለው፣ ሶስት ቤት ሙሉ በሙሉ ወድሞ ሀዘንን አለመግለጽ “እጅግ ከባድ” ነበር ሲሉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!