በሕገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ሊወጡ የነበሩ የተለያዩ አገራት ገንዘቦችና 5 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ወርቅ ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ሊወጡ የነበሩ የተለያዩ አገራት ገንዘቦች እና 5 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ወርቅ እንዲሁም ለህወሓት እና ለሸኔ የሽብር ዓላማ ማስፈጸሚያ በድብቅ ሊተላለፉ የነበሩ የመገናኛ መሣሪያዎች እና አልባሳት ከ164 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፥ ከወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በቦሌ አውሮፕልን ማረፊያ በተደረገ ጥብቅ ክትትልና ፍተሻ በተፈጨ ስጋ ተጠቅልለው በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጡ ሲሉ የተያዙትን 34 ሺህ 100 ፓውንድ፣ 27 ሺህ 170 ዩሮ ፣ 6 ሺህ 200 የስዊዝ ፍራንክ እና 400 የካናዳ ዶላር ጨምሮ 4 ሚሊየን 59 ሺህ 378 የኢትዮጰያ ብር፣ 209 ሺህ 750 የአሜሪካ ዶላር ፣ 47 ሺህ 370 ዩሮ እና 37 ሺህ 330 የእንግሊዝ ፓውንድ በወንጀሉ ከተጠረጠሩ 134 ግለሰቦች ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በተመሳሳይ 5 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ወርቅም በሕገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ሊወጣ ሲል የተያዘ ሲሆን፥ ከህገ ወጥ ድርጊቱ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 12 ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

መግለጫው እንዳብራራው፥ በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሊወጡ የነበሩ የተለያዩ አገራት ገንዘቦች በአሸባሪነት ለተፈረጁት ህወሓትና ሸኔ የውጭ ሴሎች የፋይናንስ አቅርቦት በማሟላት በኢትዮጵያ የሽብር ተግባር እንዲፈጸም እና የውጭ ምንዛሪ በማሸሽ የሀገር ኢኮኖሚ ለማዳከም የሚውሉ ነበሩ ፡፡
በተያያዘም በአሸባሪነት የተፈረጁት ህወሓት እና ሸኔ ለመፈጸም ላቀዱት የሽብር ተግባር እንዲውሉ ታቅደው በድብቅ ሊተላለፉ የነበሩ የመገናኛ መሣሪያዎች እና አልባሳት ሰሞኑን በተከታታይ በተደረጉ ክትትሎችና ፍተሻዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡

አሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ጭምር በማበር ሀገር የማፍረስ የውክልና ጦርነት ላይ ቢሰማሩም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሚመራው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም የአማራና የአፋር ፀጥታ ሃይል ሽንፈት እየተከናነቡ በመሆኑ በግንባር ያጡትን ውጤት የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የሽብር ተግባር በመፈጸም ለማካካስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ነው የጠቆመው።
መግለጫው የአሸባሪ ቡድኖቹን ህቡዕ እንቅስቃሴና የግንኙነት መረብ በመከታተል በተደረገው ጥብቅ ክትትል 13 የጂፒኤስ መሣሪያዎች፣ ዘጠኝ ሳተላይት የመገናኛ ሬዲዮኖች፣ አምስት ሳተላይት ስልኮች፣ የጦር ሜዳ መነፀር እና አልባሳት ለህወሓትና ለሸኔ የሽብር ተልዕኮ ማስፈጸሚያነት ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በድርጊቱ የተጠረጠሩ አምስት ግለሠቦችም በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛል ተብሏል፡፡
የሽብር ቡድኖቹ ‹‹አዲስ አበባን ከበናል፤ በጥቂት ቀናትም በቁጥጥር ስር እናውላታለን›› በማለት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሲነዙ እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው፥ ለዚህ ተልዕኮ እንዲውሉ ታቅደው ወደ ከተማዋ በተለያዩ ስልቶች ሊገቡ የነበሩ አልባሳቶች መያዛቸውን አስታውቋል፡፡

የሽብር ቡድኖቹ የውጭ ሴሎች በፖስታ ቤት ከተለያዩ ልብሶች ጋር በመቀላቀል የሸኔና የተቃዋሚ አመራሮች ምስል ያለባቸው ልብሶች እንዲሁም የኦነግ አርማ የታተመባቸው ቲሸርቶች፣ ኮፍያዎችና የአንገት ፎጣዎችን በተመሳሳይም የአሸባሪው ህወሓት አመራሮች ምስልና አርማ የታተሙባቸውን ቲሸርቶች በፖስታ ቤት በመላክ ለማስገባት ሙከራ ቢያደርጉም በተከናወነው ጥብቅ ክትትል መያዛቸውን አመልክቷል።
መግለጫው 250 የሚሆኑ የወታደር የሚመስሉ ልብሶችና ኮፍያዎችም በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ጠቁሟል፡፡ ከህገወጥ ድርጊቱ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 13 ሰዎችም ተይዘዋል ነው ያለው፡፡

እነዚህ አልባሳት ወደ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ለአሸባሪ ቡድኖቹ ተላላኪዎችና ናፋቂዎች ተሰራጭተው እንዲለብሱትና በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ፎት ተነስተው በማህበራዊ ሚድያ እንዲለቁት በማድረግ “አዲስ አበባን ተቆጣጥረናል” የሚል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እና የስነ ልቦና ጦርነት ለማካሄድ ታልሞ እንደነበር ነው የተጠቆመው።
እቅዱ የመረጃና የደህንነት ተቋሙ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ባከናወነው ኦፕሬሽን ከውጥኑ መምከኑን አስታውቋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በመግለጫው ከወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በአሸባሪነት የተፈረጁ ቡድኖችን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ለመግታት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ሲሆን፥ ኅብረተሰቡም እየተገኘ ላለው ውጤት ወሳኝ ሚና እያበረከተ ይገኛል ብሏል፡፡
ወደፊትም ኅብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኙ የጸጥታና ደኅንነት አካላት ጥቆማ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡