Fana: At a Speed of Life!

ከገና እና ጥምቀት በዓላት ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት የ5 ሚሊየን ሊትር ዘይት ግዥ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመጪው የገና እና ጥምቀት በዓላት ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ከውጭ ለማስገባት ግዥ እያካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ገለጸ፡፡

የድርጅቱ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ንጉሴ ገብረማሪያም እንደገለጹት÷ በአሁኑ ወቅት በተለይ በዘይት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ክፍተት እንዳይፈጠር በትኩረት እየሰራ ነው፡፡

ለአብነትም በተያዘው በጀት ዓመት መስከረም ወር 24 ነጥብ 8 ሚሊየን ሊትር ዘይት ከውጭ በማስገባት ለኀብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡን አንስተዋል፡፡

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት መጪውን የገና እና ጥምቀት በዓላት ምክንያት በማድረግ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት 5 ሚሊየን ሊትር ዘይት ከውጭ ለማስገባት ግዥ እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በዋናነት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው ያስረዱት፡፡

መንግስት በአገር ውስጥ ያሉ ዘይት አምራቾችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱን ገልጸው፥ በዚህም አሁን ላይ በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች መነቃቃት እያሳዩ እንደሆነ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአገር ውስጥ ያሉ ዘይት አምራች ድርጅቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም እስካሁን ባለው ሂደት በአገር ውስጥ ያለውን የዘይት ፍላጎት በማሟላት ረገድ ከ25 በመቶ ያነሰ ድርሻ እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.