ሰባት የሽብር ቡድን አባላትን ገድለው ጀብድ የፈፀሙት የሸዋው አርሶ አደር
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አርሶ አደር አዲስ ደስታ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ ራሳ ቀጠና የመዲና ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።
በእውር ድንብር ወደ ሸዋ ዘው ብሎ በመግባት ሊገድልና ሊያፈናቅል የመጣውን የህወሃት ወራሪ ቡድን ባላቸው ጦር መሳሪያ ተፋልመው የጀግንነት ታሪክን በክንዳቸው ጽፈዋል፡፡
ህዳር 17 ቀን 2014 ዓ.ም የጥፋት ቡድኑ ወደ ቀያቸው በገባበት ወቅት የ56 ዓመቱ እኝህ ባለታሪክ፥ “ሀገር ጀግናን በጭንቅ ጊዜ አምጣ ትወልዳለች እንዲሉ” ጠላትን አርበድብደው አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ጀብድ ፈፅመው የቁርጥ ቀን ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል፡፡
እሳቸው በወቅቱ ከማህበረሰቡ ጋር ሆነው አካባቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ ባለቡት ወቅት፥ ለቀየው እንግዳ የሆኑ ሰዎችን ተመለከቱ፤ ጥርጣሬም ይገባቸዋል። ምናልባት የወገን ጦር አባላት ከሆኑ ብለው ቢጠሯቸውም ምንም ምላሽ ሳያገኙ ቀሩ፡፡
ይህንን ለማረጋገጥ አንድ ጥይት ይተኩሳሉ፤ ለካ እነዚያ ሰዎች የሽብር ቡድኑ ህወሓት ሰላዮች ነበሩና እግሬ አውጭኝ አሉ።
ጥርጣሬያቸው ልክ ነበር፤ ፀጉረ ልውጥ የህወሓት ታጣቂዎች መሆናቸው ተረጋገጠ፡፡
ከጥቂት ቆይታ በኋላም በርካታ የጠላት ተዋጊዎች ተሰባስበው ወደ እኛ ይተኩሱብን ጀመር ይላሉ የራሳው ጀግና።
የተከፈተብንን ተኩስ ለመመከት እና ጠላትን ለማንበርከክ ወሰንኩ፤ መስዋዕትነትም ለመክፈል ተዘጋጀሁ ሲሉ ሃሳባቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አካፍለዋል፡፡
በርቀት ተኩሼ ጥይት አላባክንም፤ ወደ እርሳቸው እየቀረቡ ከመጡት ጠላቶች መካከል ኢላማ ውስጥ በማስገባት በየተራ ስድስቱን ታጣቂዎች በያዙት ክላሽ እንኮቭ መደምሰሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህን ጀብዱ እንደፈፀሙ ግን ከጠላት የተተኮሰባቸው መትረየስ እጃቸውንና መሳሪያቸውን ጭምር መታባቸው።
መሳሪያቸው ከጥቅም ውጭ ሆነ። ሰውዬው ጀግና አይደሉ፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነውም ተስፋ አልቆረጡም ነበር።
በዚህን ጊዜ አንዲት ሴት የሽብር ቡድኑ አባል ቦንብ ጣለችብኝ፤ እኔም የወረወረችብኝን ቦንብ በፍጥነት መለስኩላት ይላሉ።
እኔን ልታጠፋ የወረወረችው ቦንብ መጥፊያዋ ሆነ። “አንጀቷን ነቅሎ ጭንቅላቷ ላይ አሳረፈው”አሉን በአንደበታቸው ሲገልፁ።
በአጠቃላይ መቁጠር የቻሉትን ሰባት የሽብር ቡድኑ ህወሓት አባላትን መግደል መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ እርምጃ በኋላ አካባቢዬን በሚገባ ስለማውቀው በአቅራባዬ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ተሰወርኩ። ጠላት ሊያጠፋኝ ተኩስ ቢከፍትብኝም ነፍሴን መንጠቅ አልተቻለውም ብለዋል፡፡
ከስድስት ቀናት የጠላት ከበባ በኋላ አጥፊው ቡድን የሽንፈት ፅዋን እየመረረውም ቢሆን በመጋቱ ከቀዬው ነዋሪዎች ጋር በህይወት ተርፈው ለመገናኘት መብቃታቸውን ይገልፃሉ።
ከቡድኑ ጥቃት ተርፈው ዛሬ ላይ ‹‹ማን ያውራ የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ›› እንዲሉ ይህንን ታሪካቸውን ለደብረ ብርሃን ፋና ኤፍ ኤም አጋርተዋል፡፡
በሰላም አሰፋ
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!