የክፍለ ዘመኑ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አፍሪካን ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ነፃ የማውጣት ትግል ነው-የዓለም ባንክ አማካሪ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “የ21ኛው ክፍለ ዘመን የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አፍሪካን ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ነፃ የማውጣት ትግል ነው” ይላሉ የዓለም ባንክ አማካሪና በአትላንቲክ ካውንስል የጥናትና ምርምር ማዕከል የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪው አቶ ገብርኤል ንጋቱ።
ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሰረት፣ የአፍሪካውያን የነፃነት ቀንዲል እና በአንድነት የሚመክሩባቸው ተቋማት መስራች ናት።
አፍሪካውያንን በፀረ ቅኝ ግዛት ትግል በማስተባበር፣ በማሰልጠን እና በማማከር ትልቅ ሚና ተጫውታለች።
ከዚህም በላይ በአፍሪካዊነቷ የማትደራደር ለአፍሪካ ጥቅሞች ዘብ የቆመችና የአፍሪካን ሰንደቅዓላማ ያነሳች ናት ሲሉ አቶ ገብርኤል ንጋቱ ይገልጻሉ።
አቶ ገብርኤል ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ዋጋ የከፈለች ሃገር መሆኗን በማንሳት ሌሎች አፍሪካውያንም የኢትዮጵያን ፈለግ በመከተል የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄን ማቀጣጠላቸውን አብራርተዋል።
በ20ኛው መቶ ክፍለዘመን የነበረው የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ዋነኛ ግቡ አህጉራዊ ፖለቲካዊ አንደነትንና ነጻነትን ማምጣት እንደነበርም አስታውሰዋል።
አፍሪካውያን በአንፃራዊነት ፖለቲካዊ ነጻነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ነፃነትን ቢቀዳጁም ኢኮኖሚያ ጥገኝነቱና ጦርነቱ አሁንም አለመቀረፉን ተናግረዋል አቶ ገብረኤል።
የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አሁንም በየሀገራቱ ምሁራንና ፖለቲከኞች እንዲሁም በመንግስታት ዋነኛ አጀንዳ ሲሆን የ21ኛው ክፍለዘመን የንቅናቄው ዋነኛ ትኩረት ኢኮኖሚያዊ ነጻነት ላይ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ራሷን ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ለማላቀቅና በምግብ ራሷን ለመቻል አዲስ ምዕራፍ መጀመሯን ያደነቁት አማካሪው፥ ይህን ለማረጋገጥ አስቻይ ሁኔታዎች አሉ ብለዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ የአየር ንብረቱ ምቹነት፣ የመሬቱ ለም መሆን እና አቅሙ እንዳላት በመግለጽ።
ሀገሪቱ በምግብ ራሷን ከመቻል አልፋ ለሌሎች ሀገራትም ወደመላክ ልትሸጋገር እንደምትችል በመጥቀስ ኢኮኖሚያዊ ነፃነታችንን የማይወዱ ሀገራት ሊኖሩ እንደሚችሉም ጠቅሰዋል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ጫናዎችን ተቋቁማ ያቀደቻቸውን ከምግብና ኢንዱስትሪ ጥገኝነት ነፃ የመውጣት ጉዞዋን በማሳካት ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ማስፋፋት እንዳለባት ጠቁመዋል።
ይህን ማሳካት ከተቻለ ሌሎች አፍሪካውያንም የኢትዮጵያን አርዓያ በመከተል አፍሪካ በሁለተኛው የፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄዋ ከፖለቲካዊ ነፃነት ባሻገር ራሷን ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ነፃ ታወጣለች ነው ያሉት።
ለዚህም አካባቢያዊ ትብብርን ማጠናከር፣ አህጉራዊ የፖለቲካ ልዩነቶችን ማስወገድና የነፃ ንግድ ስምምነትን በአፋጣኝ መተግበር እንደሚገባም አንስተዋል።