ነዋሪነታቸው በአሜሪካ የሆኑት ጥንዶች በ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ያስገነቡትን ትምህርት ቤቶች አስረከቡ
አዲስ አበባ ጥር 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ነዋሪነታቸው በአሜሪካ የሆኑት ጥንዶች በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች በ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ሶሶት ትምህርት ቤቶችና ሌሎች የልማት ስራዎችን አጠናቀው ለህብረተሰቡ አስረከቡ፡፡
በአሜሪካ ሀገር የሚኖሩት አቶ ተስፋዬ አስማማውና ባለቤታቸው ወይዘሮ አስቴር እንዳለ፥ በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ የወደቁ ለደረጃ የማይመጥኑ ትምህርት ቤቶችን በማህበራዊ ትስስር ገፅ በምስል ይመለከታሉ።
አቶ አስማማው ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ሊወድቁ በተቃረቡ ትምህርት ቤቶች ህፃናት እንዲማሩ አልፈቀዱምና በነገሩ ተቆጭተው ሀሳቡን ለሚወዷት የትዳር አጋራቸው ወይዘሮ አስቴር እንዳለ ያጫውታሉ።
በወቅቱም ጥንዶቹ በሀሳቡ ተስማምተው ወደ ተግባር መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡
በዚህም መሰረትም የጎርጎራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቅዱስ ዮሐንስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና አቸርጌ ኮለኔል በላይ አስጨናቄ ትምህርት ቤቶችን በ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጪ ደረጃቸውን ጠብቀው ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
በጎርጎራና አካባቢው ዕድሜ ጠገብ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ያሉ ቢሆንም፥ ለመማር ማስተማር ምቹ ባለመሆናቸው በተማሪዎች የትምህርት አቀባበልና ውጤት ላይ ከፍተኛ ተፅህኖ ማሳደራቸውን ተማሪዎችና ወላጆች ተናግረዋል።
ከአርባ አንድ ዓመት በኃላ ወደ ትውልድ ቦታቸው የተመለሱት አቶ ተስፋዬ ከልማት ስራ ጎን ለጎንም 120 ግለሰቦችን በቋሚነት በመደገፍ ግለሰባዊ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ ነው።
በቀጣይም በትምህርት ቤቶች የተፈጠረውን የመፅሐፍት ዕጥረት ለመፍታትና ሌሎች የልማት ስራዎችን እንደሚያከናውኑ ገልፀዋል።
የጎርጎራ የተቀናጀ ልማት በጎአድራጎት ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ሂሩት ተሰማ እንደተናገሩት፥ ሁለቱ ዳያስፖራዎች በከተማውና በገጠሩ ማህበረሰብ ያለውን መሰረታዊ የልማት ችግሮች በማጤን መስራታቸው የሚመሰገን ተግባር ነው።
በምናለ አየነው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!